ተወዳጁ የቤት እንስሳ – The Favorite Pet

                                             

ከሮቤ ባልቻ

ከለማዳ የቤት እንስሳት ሁሉ ውሻ በጣም ተወዳጅ ነው፡፡ ‹‹ውሻ ታማኝ ነው፤›› ባለቤቱንና ንብረቱን ይጠብቃል፤ ከጥቃትም ይከላከላል፤›› ተብሎም በአገራችን ይሞካሻል፡፡ አብዛኞቹ የአውሮፓ አገሮችም ለውሻ ያላቸው ፍቅር ከፍ ያለ ነው፡፡ እንደ ኑሮው ሁኔታ ከአንድ እስከ ሁለትና ሦስት ውሾች ማሳደግም የተለመደ ነው፡፡

ውሻ አሳድጎ የውሻ ባለቤት መሆንና በግቢ ወይም በአፓርታማ ቤቶች አስሮ ለጥበቃ ብቻ ማስቀመጡ ለአውሮፓውያኑ በቂ አይደለም፡፡

እያንዳንዱ የውሻ ባለቤት ማታ ከሥራ መልስ ወይም ጠዋት ውሻውን በተዘጋጀለት ማሰሪያ በመቆጣጠር ሲያናፍሰውና ሲያዝናናው መመልከት የተለመደ ነው፡፡ ሥራ የሌላቸው ወይም በሥራ እረፍትና በጡረታ ላይ ያሉ የውሻ ባለቤቶች ደግሞ ባመቻቸው ሰዓት ውሾቻቸውን ይዘው ሲዘዋወሩ ይታያሉ፡፡

በክረምቱ ወራት ውሾቹ በቅዝቃዜ እንዳይጎዱ ከጀርባቸው የሚጠለቅላቸው የተዘጋጁ አልባሳት አሉዋቸው፡፡ አውሮፓውያኑ የውሾች ባለቤቶች ለውሾቹ ብቻ ሳይሆን ለአካባቢያቸው ንጽሕና መጠበቅ የሚያሳዩት ጥንቃቄም ለሚኖሩበት ከተማ ወይም ሰፈር የሚሰጡትን ትኩረት ይገልጻል፡፡

ውሾቹ አብዛኛውን ጊዜ የሚፀዳዱት በሚናፈሱበት ወቅት ስለሆነ፣ እያንዳንዱ የውሻ ባለቤት ፌስታል መሰል ላስቲኮችን በቦርሳ ወይም በኪስ ይዞ መንቀሳቀስ የተለመደ ተግባር ነው፡፡ ውሾቹ ከተፀዳዱ ባለቤቶቹ  በያዙት ማፈሻ ቆሻሻውን  አንስተው በየመንገዱና በየሰፈሩ በተቀመጡ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ መጨመር አለባቸው፡፡ ይህ ፖሊስ ወይም የሰፈር ጥበቃ ተከታትሎ የሚያስፈጽመው አይደለም፡፡ የዕድገታቸው ደረጃ ሆኖ ሕዝቡ እንደ ባህል የተቀበለው ተግባር ነው፡፡ ይህን አለማድረግ ደግሞ በጣም ነውርና ከሰው የማይጠበቅ መሆኑን ተቀብለውታል፡፡ ስለዚህ ውሾቹ ተፀዳድተው የተውትን ቆሻሻ ሰው አየኝ አላየኝ ብሎ ትቶ መሄድ አይታሰብም፡፡ ይህ የሕዝቡ ባሕል አንድ አካል ሆኗል ማለት ነው፡፡

ይህን ተግባር ስመለከት ለእኛ ለአፍሪካውያን ሁለት ቁም ነገሮችን ተመኘሁ፡፡ አንደኛው፣ አቅም ኖሯቸው የቤት እንስሳት የሚያሳድጉ ግለሰቦች ለእንስሳው የሚያደርጉት ክብካቤ መልካም ሆኖ መገኘት፡፡ ሁለተኛው፣ የመኖሪያ አካባቢዎችንና ከተሞችን ባለው አቅም እንደራሱ ጉዳይ አይቶ የሚንከባከብና የሚቆረቆርላቸው ኅብረተሰብና የከተሞች አመራሮች በብዛት ተፈጥረው ማየት፡፡

ምንጭ:- ሪፖርተር

 

Advertisement