የአሜሪካው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ስለሽግግር ሂደት ይወያያሉ – The US Minister of Foreign Affairs Will Discuss The Transition Process

                  

የአሜሪካው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሰን በኢትዮጵያ ለዓመታት ስለዘለቅው ተቃውሞና በሃገሪቱ ስላለው የፖለቲካ ሁኔታ ከባለስልጣናት ጋር እንደሚነጋገሩ ይጠበቃል።

በአፍሪካ የመጀመሪያቸው በሚሆነው በዚህ ጉብኝት አምስት ሃገራትን ይጎበኛሉ።የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ በጉዟቸው ኢትዮጵያን፣ ጂቡቲን፣ ቻድን፣ ናይጄሪያንና ኬንያን የሚጎበኙ ሲሆን ከሃገራቱ መሪዎችና ከአፍሪካ ህብረት የበላይ ኃላፊዎች ጋር ይወያያሉ።

የአሜሪካ ባለሥልጣናት እንዳሉት የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጉብኝት ትኩረት የሚያደርጉት የኢኮኖሚ ትስስርን ማሻሻል ላይ ብቻ ሳይሆን በአህጉሪቱ ውስጥ ባለው ዲሞክራሲና አስተዳደር ጉዳዮች ላይ አፅንዖት ሰጥተው ይነጋገራሉ።

አንድ የአሜሪካ ዲፕሎማት ስለውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጉዞ ሲናገሩ፣ ጉብኝቱ አሜሪካን በአፍሪካ አስደናቂ ልማት ውስጥ ተገቢውን ቦታ እንድትይዝ ለማድረግ ያለመ ነው።

የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ቲለርሰን ጉብኝት በሕዝብ ቁጥሯ ከአፍሪካ ሁለተኛ ከሆነችውና ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ካስመዘገቡ ሃገራት መካከል አንዷ ከሆነችው ከኢትዮጵያ የሚጀምር ነው።

ከሶስት ዓመታት በላይ የቆየውን ደም አፋሳሽ ፀረ-መንግሥት ተቃውሞን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በድንገት ሥልጣን ከለቀቁ በኋላ ሃገሪቱ ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ መግባቷን አመልክተዋል።

የአሜሪካን ባለሥልጣናት እንዳሉት ቲለርሰን ከኢትዮጵያ መሪዎች ጋር ስለሽግግር ሂደትና በበርካታ የሃገሪቱ ክፍሎች ስለተስተዋሉት ግጭቶች አንስተው ይወያያሉ።

ውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ በሚያደርጉት ቆይታ ከአፍሪካ ሕብረት መሪዎችን ጋር ተገናኝተው በኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ፣ በሶማሊያ እና በደቡብ ሱዳን ውስጥ ስላሉት ግጭቶች ይወያያሉ።

ተከትሎም ሚኒስትሩ ሽብርተኝነት በቀጠናው በመዋጋት እና ደህነትን በተመለከተ የአሜሪካ ስትራተጂያዊ አጋር ወደ ሆኑት ወደ ኬንያ፣ ናይጄሪያ እና ጂቡቲ የሚያቀኑ ይሆናል።

Image copyrightGETTY IMAGES

ባለሥልጣናቱ ጨምረው እንደተናገሩት ቻይና በመላው አፍሪካ በቢሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር መዋዕለ ንዋይን በመሠረተ-ልማት ላይ በማፍሰስ እየገነባች ያለውን ተፅዕኖ ለመመከት አሜሪካም በአህጉሪቱ ላይ መዋዕለ ንዋይ የመመደብ እንቅስቃሴ አንድ አካል ነው።

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በአፍሪካ የሚያደርጉት ጉብኝት የሩሲያው አቻቸው ሰርጌይ ላቭሮቭ በኢትዮጵያ፣ በአንጎላ፣ በሞዛምቢክ፣ በናሚቢያ እና በዚምባብዌ በዚህ ሳምንት ከሚያደርጉት ጉብኝት ጋር ተገጣጥሟል።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

Advertisement