የቀድሞው የድሬዳዋ-ሚኤሶ የባቡር መስመር ተጠግኖ ወደ ስራ ሊገባ ነው – The Former Dire Dawa-Mieso Railway Line is Brought into Operation

                                   

የቀድሞውን የድሬዳዋ-ሚኤሶ የባቡር መስመር በመጠገን ወደ ስራ ለማስገባት እየሰራ መሆኑን የኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር ድርጅት ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ገለፀ።

የባቡር መስመሩ እንደገና ስራ መጀመር በአዲሱ የባቡር መስመር የማይደረሱትን የምስራቁን የአገሪቱ ከተሞች ወደ መስመሩ ለማስገባት ይረዳል ተብሏል።

የድርጅቱ ዋና ስራ አስኪያጅ ተጠሪ አቶ አብዱላዚዝ አህመድ፥ ድርጅቱ ከፍተኛ ጥገናዎችን የሚያከናውኑ የጥገና ማዕከላትና የእውቀት ብቃት ያፈራ በመሆኑ የባቡር መስመሩን ጥገና በራሱ በማድረግ ወደ ስራ ለማስገባት እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

የቀድሞው የባቡር መስመር ለጥቂት ዓመታት ተቋርጦ የነበረ ቢሆንም፤ ጥገና በማድረግ ከድሬዳዋ ደወሌ በሳምንት ሶስት ጊዜ በመመላለስ ድሬዳዋ ለሚገኙ ፋብሪካዎች ጥሬ እቃ፣ በመስመሩ ለሚገኙ ከተሞችም የግብርና ምርቶችን የማቅረብ ስራ እየሰራ ነው ብለዋል።

ጥገናውን በማስፋት ከድሬዳዋ ወደ አዲስ አበባ መስመር እስከ ሚኤሶ ያለውን 150 ኪሎ ሜትር በመጠገን የመስራት እቅድ መያዙንም ነው የተናገሩት።

የባቡር መስመሩ መጠገን በዚሁ ሳቢያ ለተመሰረቱ ከተሞችና ድሬዳዋ ለሚገኙት የኢንዱስትሪ ዞኖች የትራንስፖርት አማራጭ ይሆናል ነው ያሉት።

በነዳጅ የሚሰሩ ሶስት የህዝብና ስድስት የእቃ ማመላለሻ ባቡሮች መዘጋጀታቸውንም ገልጸዋል።

ከሚጠገነው መስመር አብዛኛው በተሻለ ደህንነት ላይ እንደሚገኝ፣ መስመሮቹ በኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎች እንደሚጠገኑና ከድሬዳዋ አራት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ያለ ድልድይ ግንባታ ብቻ ከመንግስት እንደሚጠበቅ ነው አቶ አብዱላዚዝ የገለፁት።

የድሬዳዋ ምክትል ከንቲባ አቶ አብደላ አህመድ በበኩላቸው አስተዳደሩ የቀድሞውን የባቡር መስመር ከአዲሱ የባቡር መስመር ጋር ለማስተሳሰር ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልፀዋል።

ጥገናው ሙሉ በሙሉ በድርጅቱ ባለሙያዎች የሚሰራ መሆኑን ጠቁመው ይህም ወደ ገንዘብ ቢቀየር 30 ሚሊየን ብር እንደሚሆን መናገራቸውን የኢዜአ ዘገባ ያመለክታል።

የቀድሞው የባቡር መስመር ግንባታ 20 ዓመታትን ፈጅቶ በ1911 ዓ.ም ስራ የጀመረ ሲሆን፥ ስራው ከፈረንሳይ መንግስት ጋር በተደረገ ስምምነት እንደተፈጸመ ይታወሳል።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement