የሳኡዲው ንጉሥ ወታደራዊ አዛዦችን ከሃላፊነት አነሱ – Saudi Arabia Is Suddenly Shaking Up Its Military

                                         

ምሽት ላይ ይፋ በሆነ ውሳኔ ሳኡዲ አረቢያ የጦር ኃይሎች ኤታማዦር ሹሙን ጨምሮ ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዦችን ከቦታቸው መነሳታቸው ተገልፀ።

የሳኡዲው ንጉሥ ሳልማን በተጨማሪም የሃገሪቱን የምድርና የአየር መከላከያ አዛዦችን በሌሎች ተክተዋል።

ይህ ዜና የወጣው የሃገሪቱ ይፋዊ የዜና ወኪል በሆነው ተቋም በኩል ሲሆን የወታደራዊ ባለሥልጣናቱ ከሃላፊነት መነሳት ምክንያቱ ምን እንደሆነ ግን በዘገባው አልተገለፀም።

ውሳኔ የተሰማው በሳኡዲ የሚመራው ጥምር ኃይል ከየመን አማፂዎች ጋር ጦርነት ውስጥ ከገባ ሦስት ዓመት ሊሆነው በተቃረበበት ወቅት ነው።

የመከላከያ ሚኒስትር የሆኑት ልዑል ሞሃመድ ቢን ሳልማን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሃገሪቱ ውስጥ ከታዩት ለውጦችና ሹምሽሮች በስተጀርባ እንዳሉ ይነገራል።

ከወራት በፊት ልዑላንን ጨምሮ በርካታ ታዋቂ የሳኡዲ ባለሃብቶችና ሚኒስትሮች ልዑሉ በሙስናና በሥልጣን ያለአግባብ መጠቀም ላይ በከፈቱት ዘመቻ ለእስር ተዳርገው ነበር።

የሳኡዲ ዜና ተቋም እንደዘገበው ጠቅላይ ኤታማዦር የነበሩት ጄኔራል አብዱል ራህማን ቢን ሳሌህ አል-ቡንያን ከሃላፊነታቸው ከተነሱት መካከል ይገኙበታል።

ከቦታቸው የተነሱትን አዛዦች ለመተካትም በርካታ ወታደራዊ መኮንኖች ተሹመዋል።

ከወታደራዊው ሹም ሽር ባሻገር በሳኡዲ ብዙም ያልተለመደውን ሴት ሚኒስትር መሾምን ጨምሮ የተለያዩ ፖለቲካዊ ሹመቶችም ይፋ ተደርገዋል።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

Advertisement