አሜሪካ በሩሲያ ተጨማሪ ማዕቀብ ለመጣል እያሰበች ነው

                                                                                       

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በሩሲያ ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ ለመጣል እያሰበ መሆኑ ተገለፀ።

የታሰበው ተጨማሪ ማዕቀብ ከሞስኮ የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ጣልቃ ገብነት ጋር የተያያዘ ነው ተብሏል።

አጃንስ ፍራንስ ፕሬስን ዋቢ በማድረግ ፕሬስ ቲቪ እንደዘገበው፥ በመጭው ህዳር ወር 2018 በሚካሄደው የአሜሪካ አጋማሽ ምርጫ የሩሲያን ጣልቃ ገብነት ሊከታተል የሚችል ግብረ ሃይል ተቋቁሟል ነው የተባለው።

ከ2016ቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ጋር ተያይዞ በሮበርት ሚውለር የሚመራው ልዩ ምክር ቤት ማጣራቶችን እያደረገ ይገኛል።

ምክር ቤቱ በሩሲያ ግለሰቦችና ተቋማት ላይ ከምርጫው ሂደት ጋር ተያይዞ ክስ ማቅረቡን ተከትሎም፥ ፕሬዚዳንት ትራምፕና ተባባሪዎቻቸው ላይ ጫናው እየበረታ ስለመሆኑ ይነገራል።

በትራምፕ አስተዳደር የታሰበው ማዕቀብ ከምርጫው ጋር ተያይዞ የሩሲያን ተሳትፎ ለመጣራት የሚደረግ ጥረት አንድ አካል መሆኑም ነው የተነገረው።

አሁን ላይም ፕሬዚዳንት ትራምፕ ሩሲያ ላይ ከፍተኛ ጫና እያደረጉ መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ።

አሜሪካ ሩሲያን ከ2016ቱ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ጋር በተያያዘ ብትወነጅልም ሞስኮ ግን ጉዳዩን አስተበናብላለች።

የቀረበውን ውንጀላም መሰረተ ቢስ በማለት አጣጥላዋለች።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement