አርኪዮሎጂስቶች በቅርቡ ያገኙትን 4400 ዓመት እድሜ ያለው የአንዲት ሴት ካህንን መቃብር ይፋ አድርገዋል – Egypt Unveils 4,400-year-old Tomb of Ancient Priestess

                                                 

ሰሞኑን አርኪዮሎጂስቶች በቅርቡ ያገኙትን 4400 ዓመት እድሜ ያለው የአንዲት ሴት ካህንን መቃብር ይፋ አድርገዋል፡፡

የዚህች ሄትፔት የተሰኘች ካህን መቃብር የተገኘው ካይሮ አጠገብ በሚገኘው ትልቁ የኩፉ ፒራሚድ አቅራቢያ ነው፡፡ መቃብሩ በተለያዩ ያማሩ እና አሁን ድረስ ቀለማቸው ያልደበዘዘ ምስሎች የተዋበ ነው ተብሏል፡፡

አጥኚዎቹ እንካሉት ካህኗ ሴቶችን በወሊድ ወቅት ትረዳለች ተብላ ትታሰብ የነበረችው ሐቶር የተሰኘችው አማልክት ካህን ነች፡፡ ግኝቱን አስመልክተው የተናገሩት የግብፅ የጥንታዊ ቅርስ ሚኒስትሩ ካሊድ አል አናኒ፣ “ካህኗ በጣም የተከበረችና ከቤተ መንግሥት ጋርም ጥብቅ ቁርኝት እንዳላት ለማወቅ ችለናል” ብለዋል፡፡

በመቃብሩ ውስጥ ያሉት ምስሎች ሄትፔት ስታድን፣ አሳ ስታጠምድና ከልጆቿ ገፀ በረከት ስትቀበል የሚያሳዩ ትዕይንቶችን እና አንድ ዝንጀሮ በሙዚቃ ኦርኬስትራ ፊት ሲደንስ የሚያሳይ ምስሎች አሉበት ተብሏል፡፡

                                                       

በቦታው ተጨማሪ የአርኪዮሎጂ ቁፋሮዎች ለማድረግ መታቀዱም ተነግሯል፡፡

በዚህ ሳምንት የተሰማ ሌላ አስደናቂ የአርኪዮሎጂ ወሬ ደግሞ ወደ ጓቲማላ ይወስደናል፡፡

ተመራማሪዎች በጓቲማላ ደን ውስጥ ተሸፍነው የነበሩ ከ60 000 በላይ የጥንታዊ የማያ ስልጣኔ ግንባታዎችን ማግኘታቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡ በሌዘር ቴክኖሎጂ በመጠቀም የተደረገው ቅኝት በደኑ ተሸፍነው የነበሩ የጥንታዊው ስልጣኔ ቤቶች፣ ቤተ መንግሥቶች፣ ከፍ ብለው የተሰሩ ጎዳናዎችና የመከላከያ ምሽጎችን አሳይቷል፡፡ አሁን የተገኙት ግንባታዎች፣ ከዚህ ቀደም በጥንታዊው ስልጣኔ ውስጥ ይኖራሉ ተብለው የሚታሰቡትን ሰዎች ብዛት በሚሊዮኖች የሚበልጥ ያደርገዋል ተብሏል፡፡

ይሄው ሊዳር የተባው የሌዘር ቴክኖሎጂ ካምቦዲያ ውስጥም ከዝነኛው የአንኮር ዋት ቤተ መቅደሰ ስር ያለ ጥንታዊ ከተማ መኖሩን ማሳየቱን ቢቢሲ አስታውሷል፡፡

አሁን በተገኘው መረጃ ላይ በመመርኮዝ … የዛሬ 1500 ዓመታት ግድም በደቡብ አሜሪካ ገናና የነበረው የማያ ስልጣኔ፣ ከ10 እስከ 15 ሚሊየን ያህል ሰዎች ይኖሩበት የነበረ መሆኑን ማወቅ ተችሏል፡፡

ሊዳር የተባለው ቴክኖሎጂ ከአውሮፕላን ወይም ከሄሊኮፕተር ላይ በመሆን በሚለቀቅ የሌዘር ብርሃን በሚነሳ ምስል፣ ከመሬት ስር ያለን ግንባታ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ሲሆን፤ ቴክኖሎጂው በአርኪዮሎጂ ጥናት ዘርፍ አብዮት ይፈጥራል ተብሎ ተገምቷል፡፡

በመቶ አመት ቁፋሮ የማናየውን ነገር ነው ቴክኖሎጂው ያሳየን ያሉት አርኪዮሎጂስቶቹ፣ ቴክኖሎጂው አሁን ይፋ ያደረገውን ግኝት ሙሉ ለሙሉ ለማሰስም ሌላ መቶ አመት ይፈጃል ብለዋል፡፡

በደን ተሸፍኖ ማንም ያላየው ባለ 7 ፎቅ ፒራሚድና የማያ ስልጣኔን ከተሞች የሚያገናኙ ከመሬት ከፍ ብለው የተገነቡ ሰፋፊ መንገዶችም ከተገኙት ውስጥ ይጠቃሳሉ፡፡

ምንጭ፦ ቢቢሲ

Advertisement