ትራምፕ ወቅቱ “የአሜሪካ አዲስ ዘመን ነው” አሉ – State of the Union: Trump Hails ‘New American Moment’

                                                

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለኮንግረስ ባደረጉት የመጀመሪያው የፕሬዝዳንትነት ቆይታቸውና የአገሪቱ ሁኔታ የሚገልፀው ንግግር ወቅቱ ”የአሜሪካ አዲስ ጊዜ” ነው በማለት አውጀዋል።

ከዲሞክራቶች ጋር አብሮ ለመስራትም እጃቸውን መዘርጋታቸውን ተናግረዋል።

የአሜሪካ ኢኮኖሚ እያደገ ቢሆንም የትራምፕ ተቀባይነት ግን እየቀነሰ ነው። ከአንድ ዓመት በፊት የመጀመሪያውን የፕሬዝዳንታዊ ንግግራቸውን ሲያደርጉ አስተዳደራችው “አስተማማኝ፣ ጠንካራና ኩሩ አሜሪካንን” እየገነባ እንደሆነ ተናግረው ነበር።

በዚህኛው ንግግራቸው ደግሞ “የአሜሪካን ህልም ለመኖር ከዚህ የተሻለ ጊዜ የለም ” ሲሉ ለኮንግረስ አባላቱ ተናግረዋል።

የአገሪቱ ዜጎች እንደ አንድ ቡድን፣ እንደ አንድ ህዝብና የአሜሪካ ቤተሰብ አንድ ላይ መቆም እንዳለባቸው የገለፁበት የትራምፕ ንግግር 40 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በቴሌቪዥን እንደተከታተሉት ይገመታል።

የውጭ ግንኙነትን በሚመለከት ሲናገሩ ደግሞ የሰሜን ኮሪያውን መሪ ኮንነዋል።

ገደብ የለሹ የፒዮንግያንግ የኒኩሌር መሳሪያ ፍላጎት በቅርቡ የአገራቸውን ደህንነት አደጋ ላይ እንዳይጥልም አስጠንቅቀዋል።

ይህ እንዳይሆንም በከፍተኛ ደረጃ አገሪቱ ላይ ጫና እየፈጠሩ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።

ትራምፕ ከሰሜን ኮሪያ ለሸሸውና ለኮንግረሱ ያደረጉት ንግግር ታዳሚ ለነበረው ሰሜን ኮሪያዊው የመብት አቀንቃኝ ጂ ሲዎንግ ሆም ምስጋና አቅርበዋል።

በሶሪያና ኢራቅ በአክራሪ እስላማዊ ኃይሎች ተይዞ የነበረ ግዛት ሁሉ ነፃ መሆኑን የተናገሩት ትራምፕ “አይኤስ እስኪሸነፍ ትግላችን ይቀጥላል” ብለዋል።

ከእሳቸው በፊት የነበሩ ሁለት ፕሬዘዳንቶች ለኮንግረሱ መሰል ንግግር ሲያደርጉ ያተኮሩት አሜሪካ በአፍጋኒስታን በምታደርገው ጦርነት ላይ ነበር።

በአገሪቱ የደህነትና ፀጥታ ሁኔታ ማሽቆልቆሉን በማመን የአሜሪካ ጦር ኃይል ግን እንዲሁ በዋዛ የሚበገር እንዳልሆነ ተናግረዋል።

በንግግራቸው ሩሲያን ከቻይና ጋር አንድ ላይ ተቀናቃኝ ሲሉ የጠቀሷት አንድ ጊዜ ብቻ ነበር።

የማሳቹሴትስ ኮንግረስ አባልና የቀድሞ ፕሬዝዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ የቅርብ ቤተሰብ የሆነው ዲሞክራቱ ጆሴፍ ኬኔዲ የትራምፕን አንድ ዓመት የስልጣን ዘመን “በሁከት” የተሞላ ብሎታል። በስልጣን ስልጣን ዘመናቸውም አሜሪካ እየተከፋፈለች እንደሆነች ገልጿል።

ምንጭ: ቢቢሲ

Advertisement