ኦቫሪያን ካንሰር ምንድነው? – What is Ovarian Cancer?

                                                                    

ኦቫሪያን ካንሰር የሚመጣው በኦቫሪ ውስጥ ያሉ መደበኛ ህዋሳት ወደ ጤናማ ያልሆኑ ህዋሳት ሲቀየሩ እና ከቁጥጥር ውጭ ሲባዙ ነው። ኦቫሪዎች የሴቶች የመራቢያ ስርዓት አካል ሲሆኑ የሴቶች የእንቁላሎች መገኛ ናቸዉ።

ኦቫሪያን ካንሰር አብዛኛውን ጊዜ የሚከሰተው ከ 50 እስከ 65 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ሴቶች ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በቤተሰብ አባላት ላይ ይታያል።

የኦቫሪያን ካንሰር ምልክቶች ምንድናቸው?
● የሆድ እብጠት
● የሆድ መንፋት ወይም የሆድ ህመም ስሜት
● ምግብ መብላት አለመፈለግ
● ሽንት ቶሎ ቶሎ መምጣት

እነዚህ ምልክቶች የኦቫሪያን ካንሰር ባልሆኑ ሁኔታዎች ጭምር ሊከሰቱ ይችላሉ። ይሁን እንጂ እነዚህ ምልክቶች ከታዮ ሀኪምዎን ወይም ነርስዎን ማሳወቅ ይኖርብዎታል።

የኦቫሪያን ካንሰር ምርመራ ምንድን ያጠቃልላል?
● የአልትራሳውንድ ወይም ሌላ የምስል ምርመራዎች
እነዚህ ምርመራዎች በሰውነት ውስጥ ያሉ አካላትን ምስል በመውሰድ ያልተለመዱ እድገቶችን ማሳየት ይችላሉ

● የደም ምርመራዎች
የኦቫሪያን ካንሰርን ለመመርመር የሚረዱ ብዙ የደም ምርመራዎች አሉ። ለምሳሌ አንዱ የCA 125 መጠን የሚለካ የደም ምርመራ ነው። የዚህ ፕሮቲን መጠነ ከተለመደው በላይ ከጨመረ የኦቫሪያን ካንሰር ምልክት ሊሆን ይችላል።
የደም ምርመራዎቹ ዶክተሮች ቀዶ ጥገናን ማድረግ ያስፈልግ እንደሆነ ለመወሰን ይረዳሉ።

● በቀዶ ጥገና ከኦቫሪው ናሙና ወስዶ መመርመር
አንዲት ሴት የኦቫሪያን ካንሰር ተጠቂ መሆንዋ እርግጠኛ መሆን የሚቻለው በቀዶ ሕክምና ከኦቫሪው ናሙና ወስዶ በመመርመር ብቻ ነው።

የኦቫሪያን ካንሰር እንዴት ይታከማል?
ለአብዛኛዎቹ ሴቶች ካንሰሩን ለማስወገድ ቀዶ ጥገና ማድረግ የመጀመሪያው የሕክምና አማራጭ ነው።
ተጨማሪ ሕክምና ካስፈለገ በካንሰሩ የስርጭት መጠን እና በሌሎች የጤና ችግሮች ላይ ይመሰረታል።
አንዳንድ ሴቶች ከቀዶ ጥገና በኋላ ሌላ ተጨማሪ ሕክምና አያስፈልጋቸውም። ሌሎች ሴቶች ደግሞ ኪሞቴራፒን ጨምሮ ሌሎች ተጨማሪ ሕክምናዎች ሊያስፈልጋቸው ይችላል።

የሆድ ህመም ፣ የሆድ መነፋት፤ የምግብ ፍላጎት መቀነስ አብዛኛውን ጊዜ የሌሎች “ቀለል ያሉ” የጤና ችግሮች ምልክቶች ቢሆኑም በተለይ እድሜያቸው ከ 50 አመት በላይ ለሆኑ ሴቶች የኦቫሪያን ካንሰር ምልክቶች ሊሆኑ እንደሚችሉ አውቀን አስፈላጊ ምርመራ በማድረግ ጤናችን እንጠብቅ 

ምንጭ:- ዶክተር አለ(Doctor Alle)

Advertisement