የአሜሪካ ምክር ቤት አባላት ከስምምነት ላይ ደረሱ – Members of The United States Congress Reached a Consensus

                                                          

የመንግሥትን ጊዜያዊ በጀት የሚመለከተውን አዋጅ ምክር ቤቱ በማፅደቁ የተዘጉ የመንግሥት ተቋማትም ተከፍተዋል።

አዋጁ እንዳይፀድቅ ሲያደርጉ የነበሩት ዲሞክራቶች በመጨረሻ ከስምምነት ላይ የደረሱት፤ ልጅ እያሉ ወደ አሜሪካ የሄዱ ስደተኞች ጉዳይ በምክር ቤቱ ለውይይት እንደሚቀርብ በሪፐብሊካኖች ቃል ስለተገባላቸው ነው።

ሰኞ ማምሻውን አዋጁ ላይ የፈረሙት ፕሬዚዳንት ትራምፕ ግን ዲሞክራቶችን ሳይወቅሱ አላለፉም። በምክር ቤቱ ዘላቂ በጀት ላይ መስማማት ባለመቻሉ ይህ የአገሪቱን በጀት ለማራዘም የተወሰደ አራተኛ ጊዜያዊ እርምጃ ነው።

አዋጁ በ81 ለ18 በምክር ቤቱ ድምፅ እንዲሁም 266 ለ150 በተወካዮች ምክር ቤት ድምፅ ፀድቋል። በምክር ቤቱ የሪፐብሊካኖች መሪ ሚች ማኮኔል የስደተኞች ጉዳይን በተመለከተ ድርድር ለማድረግ መስማማታቸውን ተናግረዋል።

ነገር ግን ማኮኔልን በመጠራጠር መጀመሪያም ስምምነት ላይ መደረስ አልነበረበትም የሚሉ ዲሞክራቶች ድምፃቸውን አሰምተዋል።

በ2020 በምክር ቤቱ የዲሞክራቲክ ፓርቲ እጩ ፕሬዘዳንቶች ይሆናሉ ተብለው የሚጠበቁት ኤልዛቤት ዋረን፣ ኪርስተን ጊሊብራንድ፣ ኮሪ ቡከር፣ በርኒ ሳንደርስና ካማላ ሃሪስ አዋጁን በመቃወም ድምፃቸውን አሰምተዋል።

አሁን የመንግሥት ተቋማት ተከፍተዋል ነገር ግን በስደተኞችና በአገሪቱ ዘላቂ የበጀት ጉዳይ የሁለቱ ፓርቲዎች ፍልሚያ የሚቀጥል ይሆናል። ለጊዜው ግን ሁለቱም ወገኖች በተወሰነ መልኩ ድሉ የእኛ ነው እያሉ ይመስላል።

ምንጭ: ቢቢሲ

Advertisement