የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር በግማሽ ዓመት ውስጥ ከ57 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማስገኘቱ ተገለፀ – Addis Ababa Light Railway Has Secured Over 57 Million birr in Half Fiscal Year

                                                             

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር በግማሽ ዓመቱ ከ57 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማስገኘቱን የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን አስታወቀ።

ኮርፖሬሽኑ የ2010 የመጀመሪያ ግማሽ አመት የእቅድ አፈጻጸሙን ለመንግስት የልማት ድርጅቶች ቋሚ ኮሚቴ አቅርቧል።

ኮርፖሬሽኑ በግማሽ ዓመቱ በአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት 32 ሚሊዮን መንገደኞችን በማጓጓዝ 98 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት አቅዶ እንደነበር ይታወቃል።

የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ብርሃኑ ባሻህ እንደገለጹት፥ የእግረኞች ህገ-ወጥ የባቡር መስመር አጠቃቀም ባቡሮቹን ፍጥነት በማዘግየት የታሰበው ገቢ እንዳይገኝ እንቅፋት ፈጥሯል።

እግረኞች ከተፈቀዱ ሟቋረጫዎች ውጭ በባቡር መስመሮች እየገቡ ባቡሩ ከአንድ ጣቢያ ወደ ሌላኛው መድረስ ያለበትን ጊዜ እያራዘሙበት መሆኑንም ተናግረዋል።

ችግሩን ለመፍታት ሁሉም የሚመለከተው አካል በቅንጅት እንዲሰራም ጥሪ አቅርበዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ከወልድያ ሀራ ገበያ መቀሌ የባቡር ፕሮጀክት በወሰን ማስከበርና በውጭ ምንዛሬ እጥረት በታቀደው መልኩ ሊሰራ እንዳልተቻለም ገልፀዋል።

ኮርፖሬሽኑ በግማሽ ዓመቱ 12 ቢሊዮን ብር ከአገር ውስጥ ባንክ ለመበደር ቢያቅድም ማግኘት የቻለው 4 ቢሊዮን ብር መሆኑን የተናገሩት ዶክተር ብርሃኑ፤ ይህም እየተገነቡ ያሉ የባቡር ፕሮጀክቶች አፈፃፀም እንዲጓተት ማድረጉን ገልፀዋል።

የመንግስት የልማት ድርጅቶች ቋሚ ኮሚቴ በበኩሉ ኮርፖሬሽኑ ለሚያነሳቸው ችግሮች አስቀድሞ የድጋፍ ጥያቄ እንዳልቀረበለት ገልጿል።

የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ አቶ ተክሌ ተሰማ እንደተናገሩት፤ ምክር ቤቱ በቀጣይ የተገለፁ ችግሮችን ለመፍታት ከኮርፖሬሽኑ ጋር በቅንጅት ይሰራል።

ኮርፖሬሽኑ በአዲስ አበባ ቀላል ባቡር የሚስተዋሉ የእግረኞች አጠቃቀም ችግርን ለመቅረፍ ተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን መስራት እንዳለበትም አሳስበዋል።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement