NEWS: ኢትዮጵያ የውጭ ሃገር ጉዲፈቻን አገደች – Ethiopia Bans Foreign Adoptions

                                                                            

ህፃናት ጥቃት እና መገለል ይደርስባቸዋል በሚል ፍራቻ ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ሃገር የሚደረግን ጉዲፈቻን በሕግ ከለከለች።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በአሜሪካዊያን በጉዲፈቻ ህጻናት ከሚወስዱባቸው ሃገራት ኢትዮጵያ ተጠቃሽ ናት። አሜሪካዊያን በጉዲፈቻ ከተለያዩ ሃገራት ከሚወስዷቸው ህጻናት 20 በመቶ የሚሆኑትን ከኢትዮጵያ ነው የሚወስዱት።

ብራድ ፒት እና አንጀሊና ጆሊ በጉዲፈቻ ልጅ ከኢትዮጵያ ከወሰዱ ታዋቂ አሜሪካዊያን መካከል ተጠቃሾች ናቸው።

እ.አ.አ በ2013 አሜሪካዊያን ጥንዶች ከኢትዮጵያ የወሰዷትን ልጅ ገድለዋል በሚል ጥፋተኛ ተብለዋል።

ይህም ወደ ውጭ በጉዲፈቻ በሚላኩ ህፃናት ዙሪያ ክርክር እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል።

በኢትዮጵያ ያለው የጉዲፈቻ አካሄድም ቢሆን ከመብት ተሟጋቾች ብዙ ጥያቄዎች ሲያስነሳበት ቆይቷል። ሕገ-ወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ይህንን ተጠቅመው ትልቅ ገቢ እያገኙበት ነው ይላሉ።

ከሁለት ዓመት በፊት ዴንማርክ ህፃናትን በጉዲፈቻ ከኢትዮጵያ መውሰድን ከልክላለች።

ህግ አውጪዎች እንደሚሉት አሳዳጊ የሌላቸው እና ለችግር ተጋላጭ ህፃናትን በሃገር ውስጥ በሚገኝ ዘዴ መደገፍ እና መከላከል ያስፈልጋል ብለዋል።

አንዳንድ የፓርላማ አባላት ግን ወላጆቻቸውን ያጡና ለችግር ተጋላጭ የሆኑ ህፃናትን ለመርዳት ሃገሪቱ በቂ ተቋማት የላትም ብለዋል።

እ.አ.አ ከ1999 ወዲህ ከ15 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያን ህጻናት በጉዲፈቻ ወደ አሜሪካ አቅንተዋል።

ብዙዎችም እንደ ፈረንሳይ፣ ስፔን እና ጣሊያን ወዳሉ የአውሮፓ ሃገራት ተወስደዋል።

ምንጭ: ቢቢሲ

Advertisement