የኢትዮጵያ ገና ለምን ታህሳስ 29 ይከበራል? – Why do Ethiopians Celebrate Ethiopian Christmas on January 7?

                                                                    

የአውሮፓውያንን የጊዜ ቀመር በሚከተሉ ሃገራት የክርስቶስ ልደት ዲሴምበር 25 (ታህሳስ 16) ይከበራል። ኢትዮጵያዊንን ጨምሮ ከ10 በላይ ሃገራት ደግሞ ከ12 ቀናት በኋላ ታህሳስ 29 ያከብራሉ። ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ ስንል የኃይማኖት ሊቃውንትን ጠይቀናል።

የጎርጎሮሳውያን የዘመን አቆጣጠር ያመጣው ፍልሰት

የኢትዮጵያ ቤተክርስትያን የዘመን አቆጣጠር ከአውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር የተለየ ነው።

አንደኛ ሰባት ዓመት ከስምንት ወር ከአስር ቀን ልዩነት አለ። ሁለተኛ እያንዳንዱ ወር የሚይዛቸው ቀናት ልዩነት አላቸው። ”በእያንዳንዱ ወር ውስጥ ከስድስት እስከ አስር ቀናት የሚደርሱ ልዩነቶች አሉ” ይላሉ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን የዘመን ቀመር (ባህረ ሃሳብ) ዙሪያ መጽሃፍ ያሳተሙት መጋቤ ጥበብ በእምነት ምትኩ ።

“የጎርጎሮሳውያኑ የዘመን አቆጣጠር እስከተጀመረበት ድረስ መላው ዓለም ተመሳሳይ የዘመን አቆጣጠር እንደነበረው ይታመናል”የሚሉት መጋቤ ጥበብ በእምነት” ነገር ግን በ1382 ዓ.ም የካቶሊክ ቤተክርስትያን ጳጳስ የነበረው ጎርጎሪዮስ የዘመን አቆጣጠሩ ችግር አለበት በሚል እንደገና እንዲሰላ ወሰነ። ከዚያም በአንድ ዓመት ውስጥ 365 ቀን ከ6 ሰዓት ነው ያለው የሚለውን ሃሳብ በማንሳት በየዓመቱ አንድ አንድ ሰዓት ተጨምሮብናል” ይላሉ።

ስለዚህ እንደ መጋቤ ጥበብ በእምነት ይህ አንድ ሰዓት ተጠራቅሞ መጨመር አለበት በማለት ከኒቂያ ጉባኤ ጀምሮ ያለውን አስልቶ በማሳሰብ 10 ቀን በመሙላቱ ኦክቶበር 5 የነበረውን ኦክቶበር 15 ነው ሲል አውጇል።

“ስለዚህ በእኛና በእነሱ መካከል እየቀነሰ የሚሄድ ቢሆንም የ10 ቀን ያህል ልዩነት አለን።”

እንግዲህ የኢትዮጵያ ቤተክርስትያን ከኖህ ዘመን ጀምሮ የነበራትን የቀን አቆጣጠር ጠብቃ ይዛ የቀጠለችና ምንም ነገር ያላሻሻለች በመሆኑ የነበረው እንዳለ ነው ሲሉ ያስረዳሉ።

“በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ቤተክርስትያን ብቻ ሳትሆን የግብፅ ቤተክርስትያንም ምንም አይነት ማሻሻያ አላደረገችም።”

“ዘመን በአንድ ክብ ላይ አንድ ነጥቡን መነሻ አድርጎ ክቡን የመቁጠር ሂደት ነው” የሚሉት ደግሞ መጋቢ ሰለሞን አበበ ገ/መድህን ናቸው ።

ዘመን መቁጠር የጀመረው ክርስትናው አይደለም የሚሉት መጋቢ ሰለሞን ክርስትናው ከመጣ በኋላ ታላቁን ክስተት የጌታን የኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ መነሻ አደረጉ ብለዋል።

“ይህም በአንድ ክብ ላይ የትኛው ነጥብ ላይ ሄጄ ነው መቁጠር የምጀምረው እንደማለት ነው። ምክንያቱም ዞረው በሚገጥሙ በማያቋርጡ ተፈጥሯዊ ሁኔታዎች የምድርን ዙረት መሠረት አድርጎ ዘመናችን ስለሚለዋወጥ ነው የምንቆጥረው።”

ስለዚህ እንደ መጋቢ ሰለሞን በጁሊያን አቆጣጠር ለቆጠራ እንዲመቸውና እንዲሞላለት በዘፈቀደ ያስገባቸው ወደ 44 ደቂቃ እና 56 ቁርጥራጭ ሰከንዶች ተጨምረዋል።

“በኋላ ላይ ጎርጎሪዮስ ሲያርመው ከዓመታት በኋላ ተጠራቅመው እነዛ ድቃቂዎች አስር ተጨማሪ ቀናት ወልደው ተገኙ።”

ጎርጎሪዮስ እነዚህ አስር ቀናት ከናካቴው ተጎርደው ይውጡ የሚል አቋም ወሰደ ሲሉ ያስረዳሉ መጋቢ ሰለሞን።

እርማቱ ሲካሄድ ለጊዜው በዓመት፣ በአስር ዓመት የማይታሰቡ ቁርጥራጭ ደቂቃዎች ቀን በመውለዳቸው ልዩነቱ እንደፈጠረ የሚናገሩት መጋቢ ሰለሞን “እኛ እንግዲህ የጁሊያን ሳይታረም የቀረውን ይዘን በመሄዳችን በወራቱ ላይና በቀናቱ ላይ አስርም ስምንትም እንዲሁም በዓመታቱ ላይ ልዩነቶችን እየፈጠረ መጣ። ስለዚህ የመጀመሪያው ልዩነት ሲታረም የታረመውን አለማካተታችን ነው።”

                                                                          

የክርስቶስ ልደት መጽሐፍ ቅዱሳዊና ታሪካዊ መሠረቶች

እንደ መጋቤ ጥበብ በእምነት የአውሮፓውያኑ የቀን አቆጣጠር መሠረት ያደረገው በ735 ዓ.ም የተከሰተውን የሮም መቃጠልን ነው። “ከዛ ተነስተው ነው የአዲስ ኪዳን ዓመተ ምህረታቸውን የቀመሩት።”

የኢትዮጵያ ቤተ-ክርስትያን ግን እንዲህ ዓይነት ክስተቶችን መሠረት እንዳላደረገች የሚናገሩት መጋቤ ጥበብ በእምነት ምክንያቱ ደግሞ እንዲህ ዓይነት ክስተቶች የዓመት ልዩነት ሊፈጥሩ ስለሚችሉ እንደሆነ ይገልፃሉ።

“የኢትዮጵያ ቤተ-ክርስትያን ለልደተ-ክርስቶስ መነሻ የምታደርገው መጽሐፍ ቅዱስ ነው። ይኸውም የሉቃስ መጽሐፍ ምዕራፍ አንድ ላይ ቅዱስ ገብርኤል በስድስተኛው ወር ወደ ድንግል ማርያም ተላከ ይላል። ስድስት ወር ማለት ከዛ በፊት አንድ ታሪክ አለ ማለት ነው።”

“በዚያው ምዕራፍ ላይ ቅዱስ ገብርኤል ወደ ዘካርያስ ሄዶ ዮሐንስ እንደሚፀነስ ብስራት ነግሮታል። የዮሐንስ ፅንሰት ከተከናወነ ከስድስተኛው ወር በኋላ ቅዱስ ገብርኤል ወደ እመቤታችን ሄደ ማለት ነው።”

“ስለዚህ የጌታ ልደት መነሻ የሆነው የዮሐንስ ፅንሰት ወይም ልደት ነው። ዮሐንስ ደግሞ መቼ ነው የተፀነሰው የሚለውን ስናይ ዘካርያስ በቤተመቅደስ ገብቶ ያጥን ነበር ይላል። ይህ ሥርዓት ደግሞ በዓመት አንዴ የሚፈፀም ነው።”

እንደ መጋቤ ጥበብ በእምነት ያንን ጊዜ ለማወቅ ደግሞ ብሉይ ኪዳን ላይ ዘካርያስ ገብቶ ቤተ መቅደሱን ያጠነበት ቀን በሰባተኛው ወር ከቀኑም በአስረኛው ቀን ነው (ዘሌ 16፥29፣ ዘሌ 23፥27 ) የሚለውን ማየት ያስፈልጋል።

በተጨማሪም የአይሁዳውያን የቀን አቆጣጠር ደግሞ የሚጀምረው ከመጋቢት ነው። ከዚያ ተነስተን መስከረም ድረስ ስንቆጥር ሰባተኛው ወር ላይ እንደርሳለን። ስለዚህ ካህኑ ለሕዝቡ ስርየተ-ኃጢዓት የሚለምነው በመስከረም ወር ነው ማለት ነው ይላሉ መጋቤ ጥበብ።

“ስለዚህ በቤተክርስትያናችን የብስራቱ ቀን መስከረም 27 ነው። ከዛ በኋላ ደግሞ ከሦስት ቀናት በኋላ ለሚስቱ ሄዶ ነግሯት ዮሐንስ ተፀነሰ። ከዚህ ከስድስት ወር በኋላ ቅዱስ ገብርኤል ወደ እመቤታችን የሄደበትን ቀን ስንቆጥረው መጋቢት 29 ቀን ይሆናል። ከዛ ደግሞ ተነስተን ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ስንቆጥር ታህሳስ 29 ላይ እንደርሳለን” ይላሉ።

የኢየሱስ ክርስቶስን ልደት መቼ ነው በትክክል መከበር ያለበት? የሚለውን ለመመለስ ቤተ-ክርስትያን በይፋ በሚታወቅ መልኩ ልደቱን ማክበር የጀመረችው መቼ ነው? የሚለውን ማየት አስፈላጊ እንደሆነ ደግሞ መጋቢ ሰለሞን ይናገራሉ።

ቅዱስ መጽሐፍ የጌታን ልደት እንጂ የተወለደበትን ቀን አይነግረንም የሚሉት መጋቢ ሰለሞን በይፋ የተመዘገበ ታሪክ የምናገኘው በ4ኛው ምዕተ-ዓመት ላይ ነው ይላሉ።

“አንዳንዶች በሦስተኛው ምዕተ-ዓመትም የመከበሩ ምልክቶች አሉ የሚል ዘገባ ያቀርባሉ። ይህ ከሆነ በዚህ የቀን ፍለጋው ውስጥ አሁንም ልዩነቶች ተፈጥረዋል።”

የተለያዩ ምሁራን የቀን ቆጠራን ለማካሄድ ባህረ-ሃሳብም ሆነ ጎሪጎሪያውያን ወደ ኋላ ሲሄዱ ስህተት መፈፀማቸውን የሚናገሩት መጋቢ ሰለሞን፤ ከዛ ይልቅ ከኢየሱስ ልደት ጋር ያለውን ቀን ለመለየት መጽሐፍ ቅዱስን መመልከት ይሻላል ይላሉ።

ኢየሱስ በተወለደ ጊዜ የነበሩ ምልክቶች የታላቁ ቄሳር መኖር፣ የሕዝብ ቆጠራ እንዲካሄድ ማዘዙ፣ የኮከቡ መታየት (ስነ-ከዋክብት ተመራማሪዎች ወደ ኋላ ሄደው አንዲመረምሩ ስለሚያስችላቸው)፣ በይሁዳ ላይ ሄሮድስ የሚባል ንጉስ መኖሩ፣ ጴንጤናዊው ጲላጦስ በሮም ላይ ገዢ ሆኖ መሾሙ፣ እነዚህ ታሪካዊ ክስተቶችን ከመፅሐፍ ቅዱስ ውጪ ካሉ ሰነዶች ጋር አያይዘን ካየን ሁለቱም የዘመን አቆጣጠሮች ወደኋላ ተሄዶ ሲመረመሩ ስህተት አለባቸው ሲሉም ሃሳባቸውን ያጠናክራሉ።

“በጎሪጎሪዮሳውያኑ 7 ዓመት ወደ ኋላ፤ በእኛ ደግሞ 15 ዓመት ወደኋላ ተመልሶ ነው የታሪካዊ ሁነቶች የተከሰቱት የሚሉ ጥናቶች ወጥተዋል” ይላሉ መጋቢ ሰለሞን።

                                                                

የኢትዮጵያ ወንጌላውያንና ካቶሊኮች

እንደ መጋቢ ሰለሞን ከሆነ የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን ክርስትያኖች ልደት፣ ሞትና ትንሳዔን አበይት በዓላት አድርገው የሚቆጥሩ ናቸው።

“በኢትዮጵያ ውስጥ ቀደምት ክርስትና ነበር። ቀዳሚውም ክርስትና ወደ 2000 ዓመት ኖሯል። ይህ ሃገር የክርስትና ውርስና ቅርስ አለው” ይላሉ።

“…ምንም እንኳ ወንጌል አማኞች በአንዳንድ አስተምህሮዎች እና ትውፊታቸው ከቀዳሚቷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስትያን ቢለዩም ነገር ግን የጌታን ልደት በማክበሩ ላይ ያንኑ የቀዳሚውን ይዞ መሄዱን መርጠዋል” ሲሉም ያስረዳሉ።

ምክንያታቸው ደግሞ የትኛውንም ለመምረጥ ምንም የተለየ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት የለም የሚል ነው። “ይልቁንም ትውፊትን ነው የመረጥነው ማለት ነው” ብለዋል።

የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስትያን በሄደችበት ሃገር ያለውን ባህል እና አካሄድ በመከተል የእምነት ስብከቷን እንደምታካሂድ የሚናገሩት መጋቤ ጥበብ በእምነት፤ በዚህ የተነሳም የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስትያን የተለየ የቀን አቆጣጠር አትከተልም ብለዋል።

ምንጭ: ቢቢሲ

Advertisement