በእስረኞች ጉዳይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ”ያለአግባብ” ተጠቅሰዋል ተባለ – Complains About That The Ethiopian Prime Minister Has Been Mentioned Inappropriately Regarding Political Prisoners

                                                                   

የኢትዮጵያ መንግሥት የፖለቲካ እስረኞች ይፈታሉ መባሉን አስተባብሎ የተወሰኑ ፖለቲከኞች ብቻ ምህረት ይደረግላቸዋል ብሏል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ረዳት እንዳሉት የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ሲባል ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች ይፈታሉ የሚለው በስህተት የተጠቀሰ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጨማሪም የተለያዩ ሰቆቃዎች በእስረኞች ላይ እንደሚፈፀምበት ሲነገር የቆው እስር ቤት እንዲዘጋ ተወስኗል ብለዋል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል የመጀመሪያው የእስረኞች መፈታትና የማዕከላዊ መዘጋት ዜና እንደተሰማ ”የአስከፊው የጭቆና ዘመን ማብቃት ምልክት ሊሆን ይችላል” ብሎ ነበር።

ነገር ግን የማዕከላዊ እስር ቤት መዘጋት እዚያ የተፈፀሙትን አሰቃቂ ድረጊቶች መሸፈኛ መሆን የለበትም ሲልም አክሏል።

ኢትዮጵያ በሰብአዊ መብት ተከራካሪዎች እና ተቃዋሚዎች ክስ ቢቀርብባትም በሃገሪቱ የፖለቲካ እስረኞች የሉም በማለት ስታስተባብል ቆይታለች።

ማክሰኞ ዕለት የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጽህፈት ቤት በሰጠው መግለጫ “ወንጀል ፈፅመዋል ተብለው የተጠረጠሩ በአቃቢ ህግ ጉዳያቸው ተይዞ በእስር የሚገኙና የተፈረደባቸው አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት እና ሌሎች ግለሰቦች የተሻለ ሃገራዊ መግባባት ለመፍጠርና የዲሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት በማሰብ ክሳቸው ተቋርጦ ወይም በምህረት ህግና ህገ-መንግሥቱ በሚፈቅደው መልኩ እንዲፈቱ ተወስኗል” ሲል ገልፆ ነበር።

ምን ያህል ሰው መቼ ይፈታሉ የሚለው እስካሁን ግልፅ አይደለም።

ከተቃዋሚዎች ህብረት አንዱ የሆነው መድረክ መንግሥት እንዲህ አይነት ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ በሚወድቅበት ወቅት የራሱን ስህተት ለመሸፈን እና ጊዜ ለመግዣ ይጠቀምበታል ሲሉ ተናግረዋል።

የመድረክ ምክትል ሊቀመንበር የሆኑት ዶ/ር በየነ ጴጥሮስ እንደሚሉት መንግሥት ለቃሉ ታማኝ የሚሆን ከሆነ እና መነጋገሩ እና መደራደሩ ወደ ነፃና ግልፅ ምርጫ የሚወስድ ከሆነ ህብረታቸው ለመደራደር ዝግጁ ነው ብለዋል።

በተያያዘ ዜናም የጠቅላይ ሚኒስትሩን መግለጫ ተከትሎ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሆኑት ሞሳ ፋኪ ማሃመት መግለጫ ያወጡ ሲሆን ክሳቸው እየታየ ያለ እና ተፈረዶባቸው በእስር ላይ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት በምህረት እንዲሁም ክሳቸው ተቋርጦ እንዲፈቱ መንግሥት መወሰኑን አድንቀዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንን መወሰኑ እና የፖለቲካውን ምህዳር በማስፋት ሃገራዊ መግባባት ለመፍጠር የወሰደውን እርምጃ ብልህነት የተሞላበት ነው ብለውታል።

ሊቀመንበሩም መላው ኢትዮጵያውያን የትኛውም የፖለቲካ አመለካከት ሳይለያቸው የይቅር ባይነት እና የአንድነት መንፈስን ለሃገራቸው ጥቅም ሲሉ እንዲቀበሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ምንጭ: ቢቢሲ

Advertisement