“ለሴት ምሁራን የተከለከለ ኃላፊነት?”

                                                      

የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ቁጥር 45 እንደሚደርስ እየተገለፀ ነው። ከእዚህ ሁሉ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መካከል አንዱም በሴቶች ተመርቶ አያውቅም ቢባል ያለጥርጥር በአገሪቱ ለእዚህ ሃለፊነት የሚበቁ ሴቶች የሉም ወይ? የሚል ጥያቄ ይከተላል።

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቀደም ሲል በተለያየ መንገድ ባስነገረው ማስታወቂያ መሰረት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ለመሆን የውጭ ሃገር ዜጎችን ጨምሮ 22 ምሁራን አመልክተዋል። ከመካከላቸውም 13ቱ ለቀጣዩ ውድድር ቀርበዋል። የውጭ ሃገር ዜጎች እንኳ ለውድድር ራሳቸውን ሲያቀርቡ አንድም ሴት ተወዳዳሪ ኢትዮጵያዊት ምሁር የለችም።

ዩኒቨርሲቲው ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ 11 ፕሬዝዳንቶች መርተውታል። አሁን ካመለከቱት ምሁራን የሚያሸንፈው 12ኛው ፕሬዝዳንት ይሆናል። በዩኒቨርሲቲው የፕሬዝዳንትነት መንበር የወንዶች ብቻ መሆኑ ይቀጥላል ማለት ነው።

በተለያየ ዘርፍ ምርምር በማድረግ ለአገሪቱ አስተዋፆ ያበረከቱ፤ በተመሳሳይም በተለያዩ የአገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች የሚያስተምሩና ብዙ ጥናቶችን ያደረጉ ሴት ምሁራን አሉ።

ነገር ግን ከዚህ ቀደምም ሴት ምሁራን የዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ሆኑ ሲባል ብዙ አልተሰማም። ለምን?

በአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት የመሆን ውድድርስ ለምን ሴት አመልካቾች የሉም? የሚል ጥያቄ ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አቅርበን ነበር።

የዩኒቨርሲቲው ህዝብ ግንኙነት አቶ አሰማኸኝ አስረስ ብቃት ያላቸውና የትም ያሉ ምሁራን መረጃው ይደርሳቸው ዘንድ እንዲወዳደሩ ማስታወቂያው በተለያየ መንገድ እንዲነገር መደረጉንና ብቃት ያላቸው ሴቶች እንደሚበረታቱም ጭምር መገለፁን ይናገራል።

ቢሆንም ግን አንድም ሴት አላመለከተችም። በአሁኑ ወቅት ከዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ሠራተኞች (መምህራን) 15 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ሲሆኑ፤ ዩኒቨርሲቲው በታሪኩ ሴት ፕሬዝዳንት ግን ኖሮት አያውቅም።

ባለፉት ዓመታት ዩኒቨርሲቲውን በምክትል ፕሬዝዳንትነት ያገለገሉ ሴቶችም ሁለት ብቻ ናቸው። እነርሱም በፕሮፌሰር አንድርያስና በፕሮፌሰር አድማሱ ፀጋዬ የፕሬዘዳንትነት ዘመን የነበሩ ናቸው።

ዩኒቨርሲቲው ሴት ምሁራንን በብዛት ለማፍራት የተለያዩ ጥረቶች እንደሚያደርግ የሚናገሩት አቶ አሰማኸኝ፤ የመጀመሪያ ዲግሪያቸው ላይ ከፍተኛ ውጤት ባያመጡም ጥሩ ውጤት ያላቸው ሴት ተማሪዎች ተባባሪ ምሩቃን ሆነው እንዲቀጠሩ ያደርጋል።

በተጨማሪም በዩኒቨርሲቲው ሥርዓተ-ፆታ ቢሮ አማካኝነት ሴት ተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርቶችን እንዲከታተሉ ማድረግም ሌላው ሴቶችን የመደገፍ እርምጃ እንደሆነ ባለሙያው ይናገራል ።

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እስካሁን 11 ፕሬዝዳንቶች ነበሩት

ዶ/ር ሙሉነሽ አበበ በቅርቡ ፕሬዝዳንቱን በመረጠው የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለውድድር ቀርበው ከነበሩት ሰባት ተወዳዳሪዎች መካከል ብቸኛዋ ሴት ነበሩ። በመጨረሻም በውድድሩ ሦስተኛ ሆነዋል።

ዶ/ር ሙሉነሽ በአሁኑ ወቅት ዩኒቨርሲቲውን በምክትል ፕሬዝዳንትነት በማገልገል ላይ ይገኛሉ። ከዓመት ከስምንት ወር በፊት ለምክትል ፕሬዝዳንትነት ሲወዳደሩ ከነበሩት ዘጠኝ ተወዳዳሪዎች ሴቶች ሁለት ብቻ እንደነበሩ ያስታውሳሉ።

የዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንትነት በውድድር ከመሆኑ በፊት ዩኒቨርሲቲውን ለሁለት ዓመት በፕሬዝዳንትነት ያገለገሉ ዶ/ር የሺመብራት ካሳ የተባሉ ሌላ ሴት ነበሩ።

ባለን መረጃ መሰረት ዶ/ር የሺመብራት በአገሪቱ አንድ ዩኒቨርሲቲን በፕሬዝዳንትነት የመሩ ብቸኛዋ ሴት ኢትዮጵያዊ ምሁር ናቸው።

በአገሪቱ የዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዝዳንትነት መንበር ሁሌም በወንዶች የተያዘ እንደሆነ፤ ምንም እንኳ ብቃት ያላቸው ሴቶች ቢኖሩም በዚህ ቦታ ላይ ሴቶችን ለመቀበል የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ዝግጁ እንዳልሆነ ዶ/ር ሙሉነሽ ይናገራሉ።

በዩኒቨርሲቲዎች ያለው እውነታ ሴቶች ወደ አመራር እንዲወጡ የሚያመች እንዳልሆነም ያምናሉ። ሴቶች ይበረታታሉ፤ ለሴቶች ማበረታቻ አለ ቢባልም ይህ ግን በተግባር የሚታይ እንዳልሆነ ዶ/ር ሙሉነሽ ያስረዳሉ።

“እንኳን ድጋፍ ለማድረግ ድጋፍ የማያስፈልጋቸውንና ብቃት ያላቸውን ሴቶች እንኳን ለመቀበል ማህበረሰቡ ዝግጁ አይደለም። የሚፈልገው የተለመደውን ነገር ማስቀጠል ነው”ይላሉ።

ዛሬ ላይ ብቃት ያላቸውን ሴቶች በአመራር ደረጃ መቀበል ካልተቻለ በአዎንታዊ ድጋፍ ሴቶችን ማብቃት ብዙ አስርታትን እንደሚፈጅም ያምናሉ።

የቀድሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አባል የነበሩና በአሁኑ ወቅት በአሜሪካ ድህረ-ዶክትሬታቸውን በመስራት ላይ የሚገኙ ሌላ ሴት ምሁርም በአጠቃላይ በዶ/ር ሙሉነሽ ሃሳብ ይስማማሉ።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ወደ አመራር ደረጃ ለመውጣት ለሴቶች የተመቹ እንዳልሆኑና ፈተናውም ለሴቶች ከወንዶች ጋር ሲነፃፀር እጥፍ ድርብ እንደሆነ ይናገራሉ።

“መካከለኛ የሚባሉ የአመራር ደረጃዎች በሙሉ በወንዶች የተያዙ ናቸው” በማለት አጠቃላይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መዋቅሮች ምቹ አለመሆናቸውን ይገልፃሉ። ብቃት ስላላቸው ብቻ ሴቶች እነዚህን መዋቅሮች አልፈው ወደ ላይ መውጣት አዳጋች እንደሆነም ይጨምራሉ።

ደቡብ ክልል ውስጥ በሚገኝ ዩኒቨርሲቲ ያስተምሩ በነበረበት ወቅት ያጋጠማቸውን ነገር እንደ ቀላል ማሳያ ያስታውሳሉ።

“ዩኒቨርሲቲው ውስጥ ኮንፍረንስ ነበር እኔም ፅሁፍ አቅራቢ ነበርኩ። ዩኒቨርሲቲው በር ላይ ቀሚስሽ ጉልበትሽን አይሸፍንም አትገቢም ተባልኩ። ይሄ መቼ ማን ያወጣው ህግ ነው? ብዬ ስጠይቅ ከዲን በላይ ያሉ ሰዎች ተባልኩ። ከዲን በላይ ያሉት ሁሉ ወንዶች ነበሩ። በመጨረሻ ስልክ ደዋውዬ ገባሁኝ። ኋላ ላይ ዩኒቨርሲቲው እውነትም እንደዚያ ያለ ህግ ማውጣቱን ተረዳሁ”ይላሉ።

በዚያ አጋጣሚ ፅሁፋቸውን ማቅረብ ባይችሉ ኖሮ የእሳቸው ድክመት ነበር? ጉዳዩ እንደራሳቸው ድክመት እንጂ የዩኒቨርሲቲው አሰራር ያደረሰባቸው ተፅእኖ ውጤት ተደርጎ ሊታይ እንዳልነበር በርግጠኝነት ይናገራሉ።

                                                   

 

ከእንደዚህ አይነቱ የበር ላይ አጋጣሚ ጀምሮ እስከ ላይ የሴት መምህራን መንገድ አስቸጋሪ እንደሆነና በዚህ መልኩ ወደ አመራር መውጣት ደግሞ በጣም ከባድ እንደሆነ ያስረዳሉ።

አሉ የሚሏቸው የመዋቅር ችግሮች ትልቅ አይደሉም። ይልቁንም “አመራር ላይና መካከለኛ ደረጃ ላይ ላሉ ሴቶች ፈተና የሚሆኑ ትንንሽ እንቅፋቶች ናቸው። ስለዚህ ወደ ላይ ልውጣ የምትል ሴት ብዙ ትንንሽ እንቅፋቶችን ማለፍ ይጠበቅበታል”ይላሉ።

ለሴቶች አዎንታዊ ድጋፍ ይደረጋል የሚባለውም በወሬ እንጂ በተግባር የሚታይ እንዳልሆነ ይገልፃሉ። እንደሳቸው እምነት ወደ ላይ መውጣት የቻሉ ጥቂት ምሁራን ሴቶችም ብዙ እንቅፋቶችን ማለፍ የቻሉ እንጂ ከሚባለው አዎንታዊ ድጋፍ የተጠቀሙ አይደሉም።

በአሁኑ ወቅት የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ሴት ሲሆኑ ይህም በውድድር የሆነ ነው። ከአጠቃላይ አካዳሚክ ሰራተኛው ደግሞ 14 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸውን የዩኒቨርሲቲው ኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አታክልቲ ሃይለስላሴ ይናገራሉ።

ከአንጋፋዎቹ አንዱ የሆነው ጅማ ዩኒቨርሲቲም ሴት ፕሬዝዳንት ኖሮት አያውቅም። አወዳድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ሴት ምክትል ፕሬዝዳንት የሾመውም ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት ነው።

በውድድሩ ያሸነፉት ዶ/ር ፀጋ ከተማ በመማር ማስተማር ሥራ ረዥም ጊዜን ያሳለፉት በዚሁ ዩኒቨርሲቲ ስለሆነ ሁሌም በወንዶች ይያዝ ወደ ነበረው ወንበር ሲመጡ የተቀባይነት ችግር እንዳላጋጠማቸው ይናገራሉ።

ሴቶች ወደ አመራር ሲወጡ የተለያዩ ችግሮች አያጋጥሟቸውም ግን አይሉም። “በየዩኒቨርሲቲው ብቃት ያላትን ሴት ማህበረሰቡ ሳይወድ በግድ ይቀበላል”ይላሉ።

የአመራር ልምድ ፕሬዝዳንት ሆኖ ለመመረጥ ዋነኛ ጉዳይ ነው። ነገር ግን ምንም እንኳ በትምህርት ደረጃቸው የላቁ ቢሆኑ በየዩኒቨርሲቲው ለአመራርነት፤ ለምሳሌም ለዲፓርትመንት ሃላፊ ወይም ተባባሪ ዲንነት ማስታወቂያ ሲወጣ ሴት ምሁራን እንደማያመለክቱ አስተያየት የሚሰጡ አሉ።

በዚህ ምክንያት የአመራር ልምድ አለማዳበራቸው ደግሞ ለፕሬዘዳንትነት እንወዳደር ቢሉ እንኳን ከመንገድ ያስቀራቸዋል ሲሉም ያክላሉ።

እነዚህ አስተያየት ሰጭዎች በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሴቶች ወደ ፕሬዝዳንትነት ያልመጡት ሁኔታዎች ምቹ ስላልሆኑ ብቻ ሳይሆን እራሳቸውም ወደ ኋላ በማለታቸው ነው ሲሉ የሚከራከሩም አሉ።

ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ሰዎች እንደነገሩን ሴት ምሁራን ለፕሬዝዳንትነት እንዲወዳደሩ ግፊት መደረጉን ነገር ግን ሴት ምሁራኑ ፈቃደኛ ሳይሆኑ መቅረታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል። ምክንያታቸውም ምን እንደሆነ ግን አልታወቀም።

ከአዲስ አባባና መቀሌ ዩኒቨርሲቲ በተመሳሳይ በጅማ ዩኒቨርሲቲም በመማር ማስተማር ውስጥ ያሉ ሴቶች ቁጥር ከአጠቃላዩ 15 በመቶ እንደሆነ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ሴት ተማሪዎችንም ሆነ መምህራንን ለማብቃት አዎንታዊ ድጋፎች እንደሚደረጉ ያነጋገርናቸው ዩኒቨርሲቲዎች ይገልፃሉ።

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እስካሁን 11 ፕሬዝዳንቶች ነበሩት።

1. ዶ/ር ሉሲን ማት (1945-1954)

2. ደጃዝማች ካሳ ወ/ማርያም (1954-61)

3. ዶ/ር አክሊሉ ሃብቴ (1961-1966)

4. ዶ/ር ታየ ጉልላት (1966-1969)

5. ዶ/ር ዱሪ ሞሃመድ (1969-1977) (1985-1987)

6. ዶ/ር አብይ ክፍሌ (1977-1983)

7. ፕሮፌሰር አለማየሁ ተፈራ (1984-1985)

8. ፕሮፌሰር ሞገሴ አሸናፊ (1988-1993)

9. ፕሮፌሰር እሸቱ ወንጨቆ (1993-1995)

10. ፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ (1995-2003)

11. ፕሮፌሰር አድማሱ ፀጋዬ (2003-2010

ምንጭ: ቢቢሲ

 

Advertisement