በፈረንጆቹ አዲስ ዓመት አንዳንድ ስልኮች ዋትስአፕን አያስጠቅሙም – In The Coming New Year Whatsup App May not Function On Some phone’s

                                                  

በዓለም አቀፍ ደረጃ በርካታ ተጠቃሚዎች ያሉት መልዕክት መላላኪያው ዋትስአፕ በፈረንጆቹ አዲስ ዓመት መጀመሪያ ዕለት (ታህሣሥ 23) ጀምሮ በተወሰኑ የእጅ ስልኮች ላይ መስራት እንደሚያቆም እየተነገረ ነው።

እንደ ዋትስፕ ይፋዊ ድረ-ገጽ ከሆነ፤ ብላክቤሪ ስሪት ሆነው ስልኩ የሚሰራበት ሥርዓት (ኦፕሬቲንግ ሲስተም) 10 እና የዊንዶውስ ስልክ ስሪት ሆነው ስልኩ የሚሰራበት ሥርዓት 8.0 ከሆነ ስልኮቹ ከዋትስፕ መተግበሪያ ጋር መጣጣም አይችሉም።

ከእነዚህ በተጨማሪም የሚከተሉት የሞባይል ስልኮች ላይ ዋትስአፕ እንደማይሰራ ተነግሯል፤ አንድሮይድ 2.3.3 በፊት የነበሩ ስሪቶች፣ ዊንዶውስ ፎን 7፣ አይፎን 3GS ወይም አይፎን ስልክ ሆኖ ስልኩ የሚሰራበት ሥርዓት 6 ከሆነ እንዲሁም ኖኪያ ሲይምቢያን S60 ዋትስአፕን ማስጠቀም አይችሉም።

ኩባንያው ኖኪያ S40፣ እንዲሁም አንድሮይድ የአሰራር ሥርዓት 2.3.7 የሚጠቀሙ ስልኮች ዋትስአፕን ተግባራዊ ለማድረግ እንደማይቻላቸው አስታውቋል።

ይህም ማለት ምንም እንኳ እነኚህን ስልኮች የሚጠቀሙ ሰዎች መልዕክት መላክና መቀበል ቢችሉም አንዳንድ የመተግበሪያዎችን መጠቀም አይቻላቸውም።

ለምሳሌ መተግበሪያው (አፕሊኬሽን) አንድ ጊዜ ስልኩ ላይ ከተጫነ በኋላ አዲስ አካውንት መክፈትም ሆነ ለውጥ ማድረግ አይቻልም።

ኩባንያው ተጠቃሚዎች አንድሮይድ 4.0፣ ዊንዶውስ ፎን 8 እንዲሁም ኤይኦኤስ 7 እና ከዚያ በላይ የአሰራር ሥርዓትን የሚጠቀሙ ስልኮችን እንዲገዙ ያበረታታል።

የኩባንያው መረጃ እንደሚያመለክተው አሁን ላይ ከመቶ ሚሊዮን በላይ ሰዎች ዋትስአፕን በተገቢው ሁኔታ ይጠቀማሉ።

ቴሌግራምና ስናፕቻትን የመሳሰሉ ሌሎች የመልዕክት መላላኪያ መተግበሪያዎች ገበያው ላይ ቢኖሩም ዋትስአፕ በዓለማችን በጣም ታዋቂው የመልዕክት መላላኪያ መሣሪያ እንደሆነ ይታመናል።

ኩባንያው በየጊዜው ለመተግበሪያው ማሻሻያ በማድረግ ተጠቃሚዎችን ከጊዜው ጋር ለማራመድ ይሞክራል ተብሏል።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement