NEWS: የግብፁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በግድቡ ላይ ለመወያየት ወደ አዲስ አበባ ሊመጡ ነው – Egypt’s Foreign Minister is Coming to Addis

                                                     

 

የግብፁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሹክሪ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድቡ ዙሪያ ለመወያየት በሚቀጥለው ሳምንት ወደ አዲስ አበባ እንደሚመጡ ተነግሯል።

ሚኒስትሩ ለውይይቱ ወደ አዲስ አበባ እንደሚመጡ ይፋ ያደረጉት የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አህመድ አቡ ዘይድ መሆናቸውን አህራም ኦንላይን በዘገባው ጠቅሷል።

ኢትዮጵያ ግድቡን ገንብታ የኤሌክትሪክ ኃይል እንድታመነጭ የሀገራቸው ፍላጎት መሆኑን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ እና የግብፅ ግንኙነት ባለፉት ሁለት ዓመታት መጠናከሩንም አንስተዋል።

ፕሬዚዳንት አብደል ፋታህ ኤል ሲሲ በአዲስ አበባ ያደረጉት ጉብኝት፣ ከፍተኛ የጋራ ኮሚቴ መመስረት እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የጋራ መተማመንን ለመፍጠር በየጊዜው የሚያደርጓቸው የመልዕክት ልውውጦችን በማሳያነት አንስተዋል።

ቃል አቀባዩ አቡ ዘይድ አሁን የተገነባውን የሁለቱን ሀገራት ልዩ ትስስር የማጣት ፍላጎት የለንም ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ፣ የሱዳንና የግብፅ የውሃ ሚኒስትሮች 7ኛውን የጋራ ስብሰባ ከህዳር 2 እስከ ህዳር 3 2010 ዓ.ም በግብፅ ዋና ከተማ ካይሮ ማካሄዳቸው ይታወቃል።

በካይሮ የተካሄደው ስብሰባም ቀደም ሲል ጥቅምት 8 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተካሄደው የቀጠለ ሲሆን፥ ባልተቋጩ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት በማድረግ እና ጉዳዮቹን ለመቋጨት ያለመ ነበር።

እንደ የውሃ፣ መስኖ እና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ገለጻ፥ “ምንም እንኳን በጉዳዩ ላይ ስምምነት ለመድረስ ጥረት የተደረገ ቢሆንም፤ ስምምነት ላይ ሳይደረስ ቀርቷል”።

ግብፅ በማማከር አገልግሎት ውሉ መሰረት ረቂቅ የጥናት ማስጀመሪያ ሪፖርቱ እንዲስተካከል እና የሶስቱ ሀገሮች አስተያየቶች ለአማካሪ ድርጅቱ እንዲላኩ የተደረገውን ጥረት በተደጋጋሚ በመቃወሟን የገለፀው ሚኒስቴሩ፥ በዚህም ምክንያት ስምምነት ላይ መድረስ አልተቻለም ብሏል።

በመሆኑም ይህ የግብፅ አካሄድ ለጥናቶቹ መዘግየት አብይ ምክንያት መሆኑንም በመግለጫው አንስቷል።

ምንም እንኳን በካይሮው ስብሰባ ጉዳዩን መቋጨት ባይቻልም፤ የሶስቱ ሀገሮች የውሃ ሚኒስትሮች በወደፊት አቅጣጫዎች ዙሪያ ለመወያየትና እና ግንኙነታቸውን ለመቀጠል ያላቸውን ቁርጠኝነት ገልጸዋል ብሏል ሚኒስቴሩ።

የኢትዮጵያ፣ ሱዳንና የግብጽ የውሃ ሚኒስትሮች ጥቅምት 8 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስብሰባ ማድረጋቸው ይታወሳል።

ስብሰባውም በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ጥናቶችን የሚያጠኑ ሁለት ኩባንያዎችና የሶስቱ ሀገራት የቴክኒክ ኮሚቴዎች የሚመሩበትን ረቂቅ መመሪያ በማዘጋጀት ነበር የተጠናቀቀው።

የኢትዮጵያ ውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ፣ የሱዳኑ አቻቸው ሙአተዝ ሙሳ እና የግብጹ ውሃ ሃብትና መስኖ ሚኒስትሩ መሃመድ አብደል አቲ የህዳሴውን ግድብ መጎብኘታቸውም ይታወሳል።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement