አፕል የአሮጌ አይፎን ስልኮችን ፍጥነት መቀነሱን አረጋገጠ – Apple Confirms It Will Slow Down Your Old iPhones

                                                

አፕል የስማርት ኤሌክትሮኒክስ አምራች ኩባንያ የአሮጌ አይፎን ስልኮችን ፍጥነታቸው እንዲቀንስ ማድረጉን አረጋግጧል።

ኩባንያው ይህን ያደረገውም ስልኮቹ ባልተጠበቀ ሁኔታ በራሳቸው ጊዜ እንዳይዘጉ ለማድረግ ነው ብሏል።

ከዓመታት በፊት የተመረቱ አይፎን ስልኮችን የሚጠቀሙ ደንበኞች ሰሞኑን ስልኮቻቸው ፍጥነታቸው መቀነሱን በቅሬታ አቅርበዋል።

ደንበኞች ቅሬታ ያቀረቡት የስልክ የውስጥ ክፍል አገልግሎቶችን የሚያቀላጥፈውን የተሻሻለ ኢንተርናል ኦፕሬቲንግ ሲስተም (iOS) ሶፍትዌር ወደ ስልካቸው በሚጭኑበት ጊዜ ፍጥነታቸው ቀንሶ ማግኘታቸውን በመጥቀስ ነው።

በሌላ በኩል ያረጀ የአይፎን ባትሪን በአዲስ መቀየር የስልኮችን ፍጥነት እንደሚጨምር መረጃው እንዳላቸው ተናግረዋል።

ስልክ አምራቹ ኩባንያ በበኩሉ አሮጌ አይፎን ስልኮች ፍጥነታቸው እንዲቀነስ ማድረጉን በመጥቀስ፥ ይህንን ያደረገው ያልተጠበቀ የስልኮች መዘጋትን ለመከላከል እና የባትሪ አጠቃቀምን ለማሻሻል ነው ብሏል።

በአይፎን 6 እና አይፎን 7 ላይ ተመራማሪዎች ባደረጉት የምርመራ ስራ iOS 10.2.1 እና 11.2.0 የሚጠቀሙ ስልኮች ፍጥነታቸው እንዲቀንሱ መደረጉን አረጋግጠዋል።

ሆኖም ቅሬታ አቅራቢዎች የስልካችን ባትሪ 40 በመቶ ኃይል ብቻ ሲቀረው እንዳይዘጋ የሚያደርገውን ችግር ለማስቀረት ሲል አፕል የስልኮችን ፍጥነት መቀነሱ ሌላ ችግር እንጂ መፍትሄ አይሆንም እያሉ ነው።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement