በተቋማት ውዝግብ ምክንያት በየቀኑ 3 ሺህ ሊትር ወተት እየተደፋ ነው – About 3,000 Liters of Milk is Dumped Daily

                                                                   

የጀነሲስ ፋርም እና የኢትዮጵያ የምግብ የመድሃኒት እና የጤና ክብካቤ አስተዳደር እና ቁጥጥር ባለስልጣን መካከል የተፈጠረው ውዝግብ በየዕለቱ 3 ሺህ ሊትር ወተት እንዲደፋ ምክንያት ሆኗል።

የጀነሲስ ፋርም የወተት ማቀነባበሪያ በተቋማት የምርመራ ውጤት ውዝግብ ምክንያት በየቀኑ 3 ሺህ ሊትር ወተት ለመድፋት ተገዷል።

እስካሁንም ከ129 ሺህ በላይ ሊትር ወተት በባዮ ጋዝ ውስጥ ማመንጫ ውስጥ ተጨምራል።

የተደፋው ወተት በገንዘብ ሲተመን ከ3 ሚሊየን ብር በላይ ዋጋ አለው።

ባለስልጣኑ ነሃሴ 25 ቀን 2009 ዓ.ም በፃፈው የቁጥጥር ሪፖርት በጀነሲስ ፋርም የወተት ምርት ላይ ከተቀመጠው መጠን በላይ የሆነ አፍላቶክሲን አግኝቻለሁ፤ የወተት አመራረት ስርዓቱም ጥራት ላይ ጫና የሚያሳድር ነው ብሏል።

ባለስልጣኑ ይህንን ካሳወቀ ሁለት ወር ከሁለት ቀን በኋላ የጀነሲስ ፋርምን የወተት ማቀነባበሪያን ጥቅምት 28 ቀን 2010 ዓ.ም አሸገ።

የኢትዮጵያ የምግብ፣ መድሃኒት እና የጤና ክብካቤ እና አስተዳደር ቁጥጥር ባለስልጣን ከገበያ ናሙና ወስጄ ባደረኩት ምርመራ በጀነሲስ ፋርም የወተት ምርት ላይ ከፍተኛ የአፍላቶክሲን መጠን አግኝቻለሁ ይላል።

የወተት ማቀነባበሪያ ድርጅቱ ደግሞ የባለስልጣኑን ውጤት በሰማ ማግስት የወተት ምርቱን አስመርምሮ ሙሉ በሙሉ ከአፍላቶክሲን ነፃ ነው መሆኑን በምርመራ ያረጋገጠበትን ሰነድ ያቀርባል።

በዚህ መካከል ግን የማቀነባበሪያ ድርጅቱ የታሸገ ሲሆን፤ አሁን ላይ ከላሞች የሚታለበው እና ከአቅራቢዎች የሚገዛው ወተት እየተደፋ ይገኛል።

በድርጅቱ ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞች እያለቀሱ የወተቱ መደፋት እንዳሳዘባቸው እነሱም የስራ ማጣት እንደተጋረጠባቸው ይናገራሉ።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ባረጋገጠው መረጃ ስለወተት ማቀነባበሪያው መከፈት እና ስላሸገው አካል ማንነትም በሁለት የመንግስት ተቋማት መካከል ውዝግብ አለ።

በማሸጊያ ወረቀቱ ላይ ማህተሙን ያሳረፈው የኢትዮጵያ የምግብ መድሃኒት እና የጤና ክብካቤ እና አስተዳደር ቁጥጥር ባለስልጣን ብቻዬን ስላላሸግኩ ብቻየን መክፈት አልችልም የሚል አቋም አለው።

በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ ቢሮ የንግድ እና የሸማቾች ዳይሬክቶሬት ደግሞ እኔ በማሸጉ እጄ የለበትም፤ ያሸገው ባለስልጣኑ ነው ሲል የቃል ምላሽ ሰጥቶናል።

የባለስልጣኑ የስራ ሃላፊዎች ስለማቀነባበሪያው የመታሸግ ምክንያት፣ እስከመቼ ታሽጎ ይቆያል በሚለው ጥያቄ እና አገኘን ስለሚሉት የአፍላቶክሲን የምርመራ ውጤት ሲጠየቁ ዝርዝር መረጃውን በዚህ ሳምንት መስጠት አንችልም ብለዋል።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement