ስለኢትዮጵያ የቤተ ክርስቲያን ስዕሎች ምን ያህል ያውቃሉ?

 

ኢትዮጵያ ከሶስት ሺ አመታት የሚሻገር የስነ ጥበብ ታሪክ እንዳላት አጥኝዎች ያወሳሉ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ክርስትና ከፍ ያለ ሚና እንደተጫወተ የሚመሰክሩ በየአብያተ ክርስትያናቱና በየገዳማቱ ግድግዳዎች ላይ ፤ በኃይማኖታዊ ድርሳናት ውስጥ እንዲሁም በእንጨት ላይ የተሰሩ በርካታ ስዕሎች ለዘመን መደራረብ እጅ ሳይሰጡ ይገኛሉ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አለ የስነጥበብና ዲዛይን ትምህርትቤት የስነ ጥበብ ታሪክ መምህርና ተመራማሪው አበባው አያሌው ‘ኧ ግሊምስ ኦፍ ኧ ስሪ ሚሊኒያ ኦፍ ኢትዮፒያን አርት’ በተሰኘ ፅሁፋቸው እንደሚያስረዱት በሶስተኛው እና በአራተኛው ክፍለ ዘመን መባቻ አካባቢ የቅድመ ክርስትና ስነ ጥበባዊ ስኬት ተመዝግቦ ነበር።

በወቅቱ የአክሱም ስርወ መንግስት በአገር ውስጥና ከሌሎች የውጭ አገራትም ጋር የሚደረጉ የንግድ እንቅስቃሴዎች እጅጉን ስኬታማ መሆኑ በተለይም ለኪነ ሕንፃና ለቅርፃ ቅርፅ ባለሞያዎች ከፍተኛ ድጋፍ ችሮታል።

በ4ኛው ምዕተዘመን ክርስትና የአክሱም መንግስታዊ ኃይማኖት ሊሆን ከበቃ በኋላ ግን ለሙታን መታሰቢያ የሚሆኑ ምስለ-ቅርፆችን እና ግዙፍ ሃውልቶችን ማቆም አንድም ከእምነቱ አስተምህሮ ጋር የሚፃረር ሆኖ በመታየቱ፤ በተጨማሪም የአረማዊ ዘመን ልማድ ተደርጎ በመቆጠሩ የቅርፃ ቅርፅ ጥበብ እየከሰመ ሲመጣ በፋንታው ክርስቲያናዊ ስነ-ስዕል አብቧል።

ነገር ግን በአክሱም ዘመን ከተሰሩት ክርስትያናዊ ስዕሎች ብዙዎቹ በተደጋጋሚ የአብያተ ክርስትያናትና የገዳማት እድሳት ምክንያት ጠፍተዋል።

ከቅድመ ክርስትያናዊ የጥበብ ስራዎች መካከል እስካሁን ያለው ትክክለኛነቱ የተረጋገጠው ብቸኛ ስዕል የአቡነ ገሪማ የወንጌሎች የድርሳን ውስጥ ምስል ነው።

ምንጭ: ቢቢሲ

 

 

Advertisement