የምስራች ለስኳር ሕመምተኞች… ዋናው ነገር ክብደት መቀነስ ሆኖ ተገኝቷል – Weight Control and Diabetes

                                                     

(ግሩም ተበጀ)

አነስተኛ የካሎሪ መጠን ያለውን የፈሳሽ ምግብ ለ5 ወራት ያህል እንዲወሰዱ ከተደረጉ 300 ያህል የስኳር ሕመም ታማሚዎች መካከል 15 ኪሎግራም እና ከዛም በላይ የቀነሱ 86 ከመቶ ያህሉ ከሕመማቸው ድነዋል…

ሰሞኑን ከተሰሙ የሳይንስ መረጃዎች መካከል ግንባር ቀደሙ ለስኳር ሕመምተኞች የምስራች ይዟል፡፡ መረጃው ሁለተኛው ዓይነት (Type 2) የስኳር በሽታ ሊድን የሚችል ነው ይለናል፡፡ ለበርካታ ዓመታት የስኳር በሽታ በነበረባቸው 300 ያህል እንግሊዛውያን ላይ የተሰራው ሙከራ እንዳሳየው 86 ከመቶ ያህሉ ከበሽታው ድነው መድሃኒት መጠቀም አቁመዋል፡፡ በሽተኞቹ ከበሽታው የተፈወሱት የሰውነት ክብደታቸውን እንዲቀንሱ በሚል በተዘጋጀላቸው አነስኛ የካሎሪ መጠን ባለው የፈሳሽ ምግብ ሳቢያ ነው፡፡

በዚህ ሳቢያ ከ300 ያህሉ የስኳር በሽታ ታማሚዎች ከሰውነት ክብደታቸው 15 ኪሎግራም እና ከዛም በላይ የቀነሱት 86 ከመቶ ያህሉ ከስኳር በሽታው ድነዋል፡፡

ሙከራው የተካሄደባቸው የስኳር በሽታ ታማሚዎች አነስተኛ የካሎሪ መጠን ያለውን ፈሳሽ ብቻ እየወሰዱ ለ5 ወራት ቆይተዋል፡፡ በዚህም የሰውነት ክብደታቸው ቀንሷል 15 ኪሎግራምና ከዛም በላይ ክብደት የቀነሱት 86 ከመቶ ያህሉም ሙሉ ለሙሉ ከበሽታቸው ተፈውሰዋል ተብሏል፡፡

ከስኳር በሽታዋ የዳነችው የ65 ዓመቷ ኢሶቤል ሙሪ ለ17 ሳምንታ ያህል አነስተኛ ካሎሪ ያለውን ፈሳሽ ብቻ ስትወስድ ቆይታለች፡፡ በዚህም ሳቢያ 25 ኪሎግራም ቀንሳ ከስኳር በሽታዋ የተፈወሰችው ኢሶቤል “ሕይወቴን ዳግም ያገኘሁት ያህል ይሰማኛል” ማለቷን የፃፈው ቢቢሲ ነውለ፡፡

Diabetes UK የተሰኘው የበጎ አድራጎት ድርጅት በሙከራ የተገኘው ውጤት በሚሊየን የሚቆጠሩ የስኳር በሽተኞችን እንደሚረዳ ተስፋ አለኝ ነው ያለው፡፡

200 ካሎሪ ብቻ ያለው የፈሳሽ ምግቡ ሁሉንም ዓይነት ንጥረ ነገሮች ግን የያዘ ነው ተብሏል፡፡

በሙከራ ውጤቱ ላይ ተመርኩዞ የተፃፈው የምርምር ወረቀት በላንሴት የሕክምና መፅኄት ላይ እና ለዓለማቀፉ የስኳር ሕመም ፌድሬሽን ቀርቧል፡፡

ሌላኛው ሰሞኑን የተሰማ የሳይንስ መረጃ የፕላስቲክ እና ፌስታልን ጉዳይ ያነሳሳል…
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የውቅያኖሶች ጉዳይ ኃላፊ የሆኑት ሊዛ ስቬንሰን ለቢቢሲ እንደተናገሩት በውቅያኖሶች ውስጥ የሚጣለው የፕላስቲክ ቆሻሻ ጉዳይ በውቅያኖሶች ውስጥ ላለው ሕይወት ትልቅ አደጋ ደቅኗል፡፡

በኬንያ ናይሮቢ ለ3 ቀናት ያህል ሲካሄድ የሰነበተው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአካባቢ ጉዳይ ጉባዔ በዛሬው ዕለት ይጠናቀቃል፡፡

የቢቢሲ ዘገባ እንደሚለው ሐገራት ምንም አይነት ፕላስቲክ ወደ ውቅያኖሶች ውስጥ እንዳይገቡ ቢስማሙም ዛሬ ይፀድቃል የተባለው ውሳኔ የጊዜ ማዕቀፍም ሆነ የሕግ አስገዳጅነት የለውም፡፡

ቢሆንም፣ የጉባዔው ተሳታፊዎች፣ ውሳኔው በቀጣይነት ለሚወጡ ጠንካራ ፖሊሲዎች እንደመነሻ እና ለቢዝነሶችም ቁርጥ የሆነ መልዕክት የሚያስተላልፍ ነው ብለዋል፡፡ 
የአካበቢ ጥበቃ ተሟጋቾች መንግሥታት የውቅያኖስ በፕላስቲክ መበከል እያሳሰባቸው መምጣቱ አንድ ነገር ቢሆንም ብክለቱን ለማቆም መፍጠን አለብን ይላሉ፡፡

አንዳንድ የጉባዔው ተሳታፊዎች የቢዝነስ ተቋማትም ለችግሩ መላ በመፈለግ ላይ ሊሳተፉ ይገባል ሲሉ ሌሎች ደግሞ በፕላስቲክ ቢዝነስ ውስጥ ያሉቱ የፕላስቲክና ፌስታል ምርትን ለመገደብ የሚወጡ ፖሊሲዎችን ለማስቀልበስ ጥረት ሲያደርጉ ታይተዋል ብለዋል፡፡

በአንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት ተግባራዊ የሆነውን የፌስታል ምርትና ስርጭት መከልከል ተከትሎ በተለይም በኬንያ የቅርጫትና የወረቀት መያዣዎች በስፋት ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው፡፡ በቅርጫት ስራውም እጅግ በርካታ የገጠር ነዋሪዎች ተጠቃሚ እየሆኑ ነው የሚለው የቢቢሲ ዘገባ ፍራፍሬ ሻጮችም ፍራፍሬዎች በቅርጫት ውስጥ መቀመጣቸው ረጅም ጊዜ ሳይበላሹ እንዲቆዩ አድርጎልናል ብለዋል፡፡

የፕላስቲክ ቆሻሻ አንታርክቲካ ድርስ ይታያል የሚሉት አጥኚዎች በስህተት ፕላስቲኩን የሚበሉ የባህር እንስሳትም በከፍተኛ ቁጥር እየሞቱ ነው ይላሉ::

ምንጭ:- የሸገር FM 102.1 ሬዲዮ

 

Advertisement