የውጪ ምንዛሬ ለመድሃኒት እጥረት ምክንያት እየሆነ ነው – Currency Increment Brings Shortage of Medicine.

                                                     

አቶ ግሩም ፈለቀ የስኳር ህመምተኛ ሲሆን ካለፉት ሦስት ወራት ወዲህ በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች የኢንሱሊን እጥረት እንዳለ ይናገራል፡፡ ግሩም ይስማማኛል የሚለውን የኢንሱሊን አይነት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ፈልጎ ማግኝት ቀላል እንዳልሆነ በምሬት ያስረዳል፡፡

ግሩም እንደሚለው ከሆነ ዴንማርክ ሰራሽ የሆነውን ‘ኢንሱላታርድ’ የተባለውን የኢንሱሊን አይነት በግል መድሃኒት ቤቶች ውስጥ በ130 ብር ይገዛ ነበር፤ አሁን ግን የብር የመግዛት አቅም እንዲቀንስ ከተደረገ በኋላ ፈልጎ ማግኘት የማይታሰብ ሆኗል። ከተገኘም እሰከ 175 ብር ድረስ ነው የሚሸጠው ሲል ያስረዳል፡፡

ቢቢሲ በግል እና ከነማ ተብለው በሚታወቁት የመንግስት መድሃኒት ቤቶች ውስጥ የተጠቀሱት ዓይነት መድሃኒቶች አቅርቦት ምን እንደሚመስል ለማጣራት ሙከራ አድርጓል እጥረት እንዳለ ለመረዳት ችሏል።

ባለሙያዎች እንደሚገልጹት የመድሃኒት አምራቾች መድሃኒቶችን ለማመረት የሚጠቀሙባቸው የተለያዩ የምርት ሂደቶች ለአንድ ዓይነት መድሃኒት የተለያዩ የምርት ዓይነቶች (ብራንዶች) እንዲኖር ያደርጋል፡፡

ለምሳሌ በሀገራችን በተጠቃሚዎች ዘንድ የተለመዱ ከአምስት ያላነሱ የኢንሱሊን የምርት ዓይነቶች አሉ፡፡

በተለያዩ ቦታዎች ተዘዋውረን ባደረግነው ማጣራት በግል መድሃኒት ቤቶች ውስጥ የትኛውንም የኢንሱሊን የምርት ዓይነት ማግኘት እጅግ አዳጋች እንደሆነ ማረጋገጥ ችለናል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ከልብ ህመም ጋር ተያያዥነት ያላቸውን መድሃኒቶች በሚፈለገው የምርት ዓይነት እና መጠን ማግኘት ከባድ ነው፡፡

ለምሳሌ የልብ ህመም ለማከም ከሚረዱት መድሃኒቶች መካከል ‘ናይፌዴፒን’ የተባለውን መድሃኒት በ20 ሚሊግራም ማግኝት አይታሰብም ሲሉ የመድሃኒት ቅመማ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

እጥረት ያጋጠማቸው መድሃኒቶች

በግል መድሃኒት ቤት ያገኘናቸው ባለሙያዎች እንደሚሉት ከሆነ አቅም ያላቸው ተጠቃሚዎች የኢንሱሊን ምርቶችን ከዱባይ ድረስ ያስመጣሉ፡፡

በሌላ በኩል በመንግሥት መድሃኒት ቤቶች ውስጥ የተለያዩ ዓይነት ምርቶችን በብዛት እና በዓይነት ማግኘት ባይቻልም ኢንሱሊንም ሆነ ለልብ ህመም የሚወሰዱ መድሃኒቶችን ማየት ችለናል፡፡

በመንግሥት መድሃኒት ቤት ባለሙያ የሆነችው ብዙነሽ ከበደ* (ስሟ የተቀየረ) እንደነገረችን አብዛኛውን ጊዜ ተጠቃሚዎች የለመዱትን የመድሃኒት ምርት ዓይነት ብቻ ነው መጠቀም የሚፈልጉት፡፡

ለምሳሌ ከተለያዩ የኢንሱሊን የምርት ዓይነቶች አሉ ትላለች ብዙነሽ። ከእነዚህ መካከል በብዛት የተለመደው ‘ኢንሱላታርድ’ የተባለው ነው፡፡

ይህ ምርት አሁን በገበያ ላይ በቀላሉ ማግኘት አይቻልም፤ ይሁን እንጂ እሱን ሊተካ የሚችል ሌላ መድሃኒት ቢኖርም ተጠቃሚው ስላልለመደው ገዝቶ መጠቀም አይፈልግም፡፡

አብዛኛውን ጊዜ ተጠቃሚዎች ሌላ አማራጭ እያላቸው ‘መድሃኒት ጠፋ’ ሲሉ ያማርራሉ ትላለች፡፡

ብዙነሽ ይህን ትበል እንጂ አቶ ግሩም ፈለቀ ግን በዚህ አይስማሙም፡፡ አቶ ግሩም ”ለኔ የሚስማማኝ ዴንማርክ ሀገር የሚሰራው ‘ኢንሱላታርድ’ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ በፊት እሱኑ ፈልጌ በማጣቴ የተለየ ምርት ተጠቅሜ ችግር ውስጥ ገብቼ ነበር” ሲሉ ይናገራሉ፡፡

                                                        

”የኢንሱሊን እጥረት በተደጋጋሚ ስለሚያጋጥም የምርት ጊዜያቸውን በመመልከት በብዛት ገዝቼ በማቀዝቃዣ ውስጥ እያስቀመጥኩ እጠቀም ነበር፡፡ አሁን መድሃኒቴን በመጨረሴ ነው እየተቸገርኩ ያለሁት” ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

እጥረቱ ለምን ተከሰተ?

በተደጋጋሚ የመድሃኒት እጥረት እንደሚከሰት ያነጋገርናቸው ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሰዎች ይስማማሉ፡፡

ሰሞኑን የኢንሱሊን እና ከልብ ህመም ጋር ተያያዥነት ያላቸው መድሃኒቶች እጥረት ለምን ተከሰተ? ለሚለው ጥያቄ መልስ ለማግኘት በኢፌዲሪ የመድሃኒት ፈንድ እና አቅርቦት ኤጀንሲ፣ የመድሃኒት አስመጪዎችን፣ የመድሃኒት ጅምላ አከፋፋዮችን እና የኢትዮጵያ ስኳር ህመም ማህበርን አነጋግረናል፡፡

ቢቢሲ የኩባንያቸው እና የእሳቸው ስም እንዲጠቀስ ያልፈለጉ በመዲናችን ግዙፍ ከሚባሉ መድሃኒት አስመጪ ኩባንያዎች መካከል የአንዱን ምክትል ዳይሬክተርንም ማነጋገር ችሎ ነበር፡፡

ምክትል ዳይሬክተሩ እንደሚሉት ”በአጠቃላይ በመድሃኒት ዙሪያ ያለው ዋነኛው ችግር የውጪ ምንዛሬ እጥረት ነው፡፡”

ከዚህ በፊት ኢንሱሊን እና ሌሎች ጊዜ የማይሰጡ የሚባሉ መድሃኒቶችን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት አስፈላጊውን መስፈርት ካሟላን ብሔራዊ ባንክ የውጪ ምንዛሬ እንድንወስድ ይፈቀድ ነበር፤ አሁን ግን ባለው እጥረት ምክንያት ይህ እንዲቀር ተደርጓል” ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

ምክትል ዳይሬክተሩ ”በዚህ የስራ መስክ ላይ ከተሰማራው በርካታ ዓመታት አስቆጥሬያለው እሰካሁን ግን ወደ ሃገር ውስጥ መድሃኒት ማስገባት እንዲህ ከባድ ሆኖ አይቼ አላውቅም” ይላሉ፡፡

                                                           

ኢሹ ሜድ በከተማችን ከሚገኙ የመድሃኒት ጅምላ አካፋፋዮች መካከል አንዱ ነው፡፡ በድርጅቱ ውስጥ ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገው የሽያጭ ባለሙያ በከተማው ውስጥ የተለያዩ የመድሃኒት አይነቶች እጥረት እንዳለ ጠቅሶ የብር የመግዛት አቅም እንዲቀንስ ከተደረገ በኋላ በህጻናት ወተት ላይም የዋጋ ጭማሪ መታየቱንም ይናገራል፡፡

እንደሽያጭ ባለሙያው ከሆነ ከዚህ ቀደም በርካታ የጅምላ አከፋፋዮች ለመድሃኒት ቤቶች ምርቶችን በብድር ያቀርቡ ነበር፤ አሁን ግን የእጅ በእጅ ክፍያን ስለሚመርጡ እጥረቱ የተከሰተበት አንዱ ምክንያት ይህ ሊሆን ይችላል ይላል፡፡

በኢፌዲሪ የመድሃኒት ፈንድ እና አቅርቦት ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ተስፋሚካኤል አፈወርቅ እንደሚሉት የመድሃኒት ፈንድ እና አቅርቦት ኤጀንሲ መድሃኒቶችን የሚያቀርበው ለመንግስት ሆስፒታሎች እና መድሃኒት ቤቶች ነው፤ ስለዚህ መድሃኒቶቹን በመንግስት ተቋማት ውስጥ ማግኘት ይቻላል፡፡

የግል አስመጪዎች ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት ባለመቻላቸው ጫናው በመንግስት ላይ ብቻ እንዲሆን አድርጎታል ይላሉ፡፡ አቶ ተስፈሚካኤል እንደሚሉት ኤጀንሲው ከአሁንም በኋላ ለ11 ወራት ያክል የሚሆን በቂ ክምችት አለው ይላሉ፡፡

በሰው ችግር ለማትረፍ የሚፈልጉ ነጋዴዎች

ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ ሌላ የኤጀንሲው ሰራተኛ ግን ከተማው ውስጥ ለሚስተዋለው አጠቃላይ የመድሃኒት እጥረት ዋነኛው ምክንያት ሌላ ነው ይላል፡፡

”የግል አስመጪዎች እና አከፋፋዮች ዶላር ላይ ጭማሪ ከመደረጉ በፊት ባስገቧቸው ምርቶች ላይ ጭማሪ አድረገው መሸጥ ስለሚፈልጉ ነው፡፡ የምርት ግዜያቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት አቆይተው የመንግስት ክምችት ሲያልቅ ጠብቀው በውድ ዋጋ ይሸጡታል፤ ይህንም በቅርብ ወራት ውስጥ የምናየው ይሆናል” ይላል፡፡

ይህ ግለሰብ እንደሚለው መድሃኒት ከውጪ ለማስገባት ከ2-3 ወራት ድረስ ይፈጃል፤ ይህ ማለት ደግሞ አሁን ሀገር ውስጥ የሚገኙት መድሃኒቶች የብር የመግዛት አቅም እንዲቀንስ ከመደረጉ በፊት የገቡ ናቸው ሲል ይሞግታል፡፡

የኢንሱሊን እጥረት የኢትዮጵያ ስኳር ህመም ማህበር አጋጥሞት ከሆነ ጠይቀን ነበር፡፡ አቶ አዝማች ፀጋዬ በኢትዮጵያ ስኳር ህመም ማህበር የፕሮጀክት ፋይናንስ ሃላፊ እና አስተዳዳሪ ናቸው፡፡ እንደ አቶ አዝማች ከሆነ ማህበራቸው የኢንሱሊን እና ተያያዥ መድሃኒቶችን ዴንማርክ ሀገር ከሚገኘው ድጋፍ ሰጭያችው ኩባንያ በቀጥታ ወደ ሀገር ውስጥ ገብቶ ስለሚቀበሉ ምንም አይነት የኢንሱሊን እጥረት አልገጠመንም ይላሉ፡፡

በቅርቡ ዓለም-አቀፉ የስኳር ህመም ፌዴሬሽን ባወጣው ሪፖርት ኢትዮጵያ 2.6 ሚሊዮን የስኳር ህመምተኞችን በመያዝ ከሰሃራ በታች ከሚገኙ ሀገራት ቁጥር አንድ ሆናች፡፡

የፌዴሬሽኑ ሪፖርት እንደሚያሳየው ከነዚህ ታማሚዎች መካከል ቢያንስ 46 በመቶ የሚሆኑት የህክምና አገልግሎት አያግኙም አሊያም በምርመራ ህመማቸውን ለይተው አላወቁም፡፡

የፌዴሬሽኑ ሪፖርት እንደሚያሳየው በዓለም ዙሪያ በ2045 የህመሙ ተጠቂዎች በ162 በመቶ ይጨምራል፡፡

 

ምንጭ: ቢቢሲ

 

Advertisement