የሳይንስ መረጃዎች: በፍጥነት መብላት ለጤና ችግር ያጋልጣል፤ ከጥልቁ ሕዋ የመጣው እንግዳ አለት ጉዳይ እና ነፍሰጡር ሴቶች በተለይ በእርግዝና የመጨረሻዎቹ 3 ወራት በጀርባ አትተኙ መባሉ::

                                                   

ሰሞኑን የወጣ አንድ ጠጥናት ውጤጥ በችኮላ መብላት ለክብደት መጨመር፣ ለአለቅጥ መወፈርና ለልብ ሕመም አጋላጭ ነው ይለናል፡፡ “ለጤናዎ ካሰቡ ረጋ ብሎ መብላትን የአመጋገብ ስልትዎ ሊያደርጉ ይገባል” ያሉት የጥናት ቡደኑ አባል ታካዩኪ ያማጂ፣ “ሰዎች ቶሎ ቶሎ በሚበሉበት ጊዜ መጥገባቸውን ልብ ስለማይሉ ከሚበቃቸው በላይ ይበላሉ” – ከዚህም በተጨማሪ ይላሉ አጥኚው – ቶሎ ቶሎ መብላት ለግሎኮስ መዋዠቅ እና ለተያያዥ የጤና ቀውስ ያጋልጣል…

ያማጂ እና የጥናት ቡድኑ ባልደረቦች አማካይ እድሜያቸው 51.2 አመት የሚሆናቸውን 642 ወንዶችና 441 ሴቶችን የአመጋገብና የጤና ሁኔታ በአምስት አመታት የጊዜ ልዩነት ውስጥ ተመልክተዋል፡፡

እ.ጎ.አ በ2008 ጥናቱ የተካሄደባቸው ሰዎች በሞላ ምንም አይነት ከአመጋገብ ጋር የተያያዘ የጤና እክል አልነበረባቸውም፡፡ ሰዎቹም ለአጥኚዎቹ የአመጋገብ ፍጥነታቸውን ነግረዋቸው ነበር፡፡ በዚህም መሰረት አንዳንዶቹ የአመጋገብ ፍጥነታቸውን ከፍተኛ ሲሉት፣ ሌሎች ደግሞ መካከለኛ፣ የተቀሩትም በጣም በቀስታ ተመጋቢዎች ሲሉ ተናግረው ነበር…

አጥኚዎቹ ከ5 ዓመታት በኋላ ተመልሰው ሲመጡ ከፈጣን ተመጋቢዎቹ 11.6 ፐርሰንቱ ከአመጋገብ ጋር ተያያዥ ለሆነ ችግር ሲጋለጡ፣ ከመካከለኛ ፍጥነት ተመጋቢዎች ግን 6.5 ፐርሰንት ያህሉ ብቻ ናቸው ከአመጋገብ ጋር ተያያዥ ለሆነ ችግር የተጋለጡት፡፡

በአንፃሩ ግን በቀስታ ከሚመገቡት መሃል ከአመጋገብ ጋር በተያያዘ ለሚመጡ በሽታዎች የተጋለጡት እጅግ አናሳ 2.3 በመቶ ያህሉ ብቻ ናቸው፡፡

ከዚህ ቀደም የተሰሩ ጥናቶችም በፍጥነት መመገብ ለክብደት እና ለደም ውስጥ ስኳር መጨመር እንደሚያጋልጡ ማሳየቱ ተጠቅሷል፡፡

አጥኚዎቹ … በሩጫ በተሞላው ዘመናዊ አኗኗችን ሳቢያ ባህል እያደረግነው የመጣነው የችኮላ አመጋገብ ነገር ለጤና ጠንቅ ነውና ልብ ያለው ልብ ይበል ማለታቸውን የዘገበው ሳይንስ አለርት ድረገፅ ሲሆን የምርምር ውጤቱ በአሜሪካ የልብ ማህበር የ2017 የሳይንስ ጉባዔ ላይ ይቀርባል ተብሏል

በዚህ ሳምንት የወጣ ሌላኛው የሳይንስ መረጃ ደግሞ ከሌላ የኮኮብ ስርዓት ወደ ፀሀይ ስርዓታችን እንደመጣ የተነገረለት እንግዳ ቅርፅ ያለው የሕዋ አለት ጉዳይ ነው…

ርዝመቱ የስፋቱን 10 እጥፍ ይሆናል የተባለለት ይህ የሕዋ አለት ኦሟሟ የሚል ስም ተሰጥቶታል – በሐዋይ ሰዎች ቋንቋ “ከሩቅ ሐገር ቀድሞ የደረሰ መልዕክት” ማለት ነው ይለናል የናሽናል ጂኦግራፊ ድረገፅ ዘገባ…

የፀሐይ ስርዓታችንን በሰዓት 98 000 ማይል በሆነ ፍጥነት እየተምዘገዘገ በማቋረጥ ላይ ያለው ይህ አለት በምድራችን አጠገብ ያለፈው ባለፈው ወር ነበር፡፡

ሳይንቲስቶች ከሕዋ አለቱ የጉዞ አቅጣጫ እና ፍጥነት በመነሳት ነው አለቱ ከፀሐይ ስርዓታችን ውጪ ከጥልቁ ሕዋ መምጣቱን የተረዱት፡፡

የሕዋ አለቱ በሌላ ኮከብ ዙሪያ ባለ የፕላኔት አፈጣጠር ሂደት አምልጦ ተወርውሮ የወጣ አለት ይሆናል ተብሎ ተገምቷል፡፡

ሌላው በዚህ ሳምንት የተሰማው የሳይንስ መረጃችን ደግሞ ነፍሰጡር ሴቶች በተለይም በእርግዝናቸው የመጨረሻ 3 ወራት በጎናቸው እንዲተኙ መመከሩን ይነግረናል፡፡

ሳይንቲስቶች እንደሚሉት በእርግዝና የመጨረሻዎቹ 3 ወራት በጀርባ መተኛት የሞተ ልጅ ለመገላገል ሊዳርግ ይችላል፡፡

በአንድ ሺ ነፍሰጡር ሴቶች ላይ የተደረገው ጥናት እንደጠቆመው በእርግዝና የመጨረሻ 3 ወራት በጀርባ መተኛት የሞተ ልጅ የመውለዱን አደጋ እጥፍ ያደርገዋል…

ነፍሰጡር ሴቶች እንቅልፍ ይዟቸው የሚተኙበት ሁኔታ ወሳኝ ነው – በጎናቸው ሊተኙ ይገባል ያሉት አጥኚዎቹ፤ “ግን ከእንቅልፍ ሲነቁ ራሳቸውን በጀርባቸው ተኝተው ካገኙት ግን ሊጨነቁ አይገባም” ብለዋል

ምንጭ:- የሸገር FM 102.1 ሬዲዮ

Advertisement