ስንቶቻችን የኮሞሮሱን የአውሮፕላን አደጋ እናስታውሳለን? – Remembering Ethiopian Airlines Crash In The Comoros Island

                                           

በደቡብ ምስራቅ አፍሪካ የምትገኘው የኮሞሮስ ደሴት ተመራጭ የጎብኚዎች መዳረሻ ስፍራ ነች።

በህንድ ውቅያኖስ ዳርቻ ሲዝናኑ የነበሩ ጎብኚዎች እና የአካባቢው ነዋሪዎች ህዳር 14/1989 ዓ.ም ግን ያልተጠበቀ ነገር ተመለከቱ።

ይህንን አሳዛኝ አጋጣሚም በካሜራቸው ቀርጸው ማቆየት የቻሉም ነበሩ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ቁጥር ET961 ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ 175 መንገደኞችን አሳፍሮ በመጓዝ ላይ ሳለ ሶስት ኢትዮጵያን ወደ አውሮፕላኑን መቆጣጠሪያ ክፍል(cockpit) በኃይል በመግባት አብራሪዎቹ የበረራ አቅጣጫቸውን ወደ አውስትራሊያ እንዲያደርጉ አስገደዱ።

አቅጣጫውን እንዲቀይር የተደረገው አውሮፕላን ለአራት ሰዓታት በአየር ላይ ከቆየ በኋላ ነዳጅ ጨርሶ በኮሞሮስ ደሴት ላይ ተከሰከሰ።

ግዙፉ ቦይንግ 767 በሰዓት 324 ኪሎ ሜትር ፍጥነት በመብረር ላይ እያለ ነበር አካሉ ከውሃው ጋር የተጋጨው። ይህም የአውሮፕላኑ አካል ተሰባብሮ በርካቶች ህይወታቸውን እንዲያጡ ምክንያት ሆኗል።

ዋና አብራሪው ካፒቴን ልዑል አባተ እና ምክትል አብራሪ የነበሩት ካፕቴን ዮናስ መኩሪያ ሊደርስ የነበረውን ከፍተኛ የሰው ህይወት መጥፋት ባደረጉት ጥረት በማዳናቸው ከበርካቶች ሙገሳ ቀርቦላቸዋል።

የበረራ ሰራተኞችን ጨምሮ 125 ሰዎች ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን 50 የሚሆኑት ደግሞ ቀላል እና ከባድ የአካል ጉዳት አስተናግደው በህይወት ተርፈዋል።

                                                    

በህይወት ከተረፉት መካከል አቶ አስመላሽ ስብሃቱ ይገኙበታል።

ዛሬ ላይ አቶ አስመላሽ የ83 ዓመት የዕድሜ ባለጸጋ ቢሆኑም የዛሬዋን ቀን 21ኛ ዓመት የልደት በዓላቸው አድርገው ነው የሚያከብሩት።

የአቶ አስመላሽ ልጅ ወ/ሮ ኤደን አስመላሽ ”አባታችን ከአደጋው በመትረፉ እንደገና እንደተወለደ አድርገን ነው የምናስበው” ትላለች።

”በህይወት በመትረፉ ለእኛ ከፍተኛ ደስታ የነበር ቢሆም እሱ ግን የተደበላለቀ ስሜት ነው የተሰማው። ቀኑን ሲያስብ በአደጋው ህይወታቸውን ያጡትን ያስባል። በሌላ በኩል ደግሞ በህይወት መትረፉ ያስደስተዋል” ስትል ታስረዳለች።

”በአደጋው ህይወታቸውን ያጡት ህጻናት በህይወት ቢኖሩ ይሄኔ ትምህርታቸውን ያጠናቅቁ ነበር” እያለ ያብሰለስላል ትላለች ኤደን ስለ አባቷ ስትናገር።

አቶ አስመላሽ በአውሮፕላኑ ክፍት ቦታ ባለመኖሩ መጓዝ እንደማይችሉ ተነግሯቸው ነበር። ሆኖም የአየር መንገዱ የረዥም ጊዜ ደንበኛ ስለሆኑ ወንበር ተፈልጎ እንደተገኘላቸው ትናገራለች። አቶ አስመላሽ ጉዞ ከመጀመራቸው በፊትም የረዥም ጊዜ ጓደኛቸውን በአውሮፕላኑ ውስጥ አግኝተው ቦታ በመቀየር ጓደኛቸው ጋር እንደተቀመጡ ትናገራለች።

የዕድል ነገር ሆኖ የአቶ አስመላሽ ጓደኛ በህይወት መትረፍ አልቻሉም።

በሶስት ኢትዮጵያውያን የተጠለፈው አውሮፕላን ከአዲሰ አበባ የተነሳው ናይሮቢ የሚያደርሰውን ነዳጅ ብቻ ሞልቶ ነበር። ይሁን እንጂ ጠላፊዎቹ ወደ አውስትራሊያ እንዲበር በማስገደዳቸው ነዳጁ እስኪያልቅ በአየር ላይ ለአራት ሰዓታት ቆይቷል።

አብራሪውና ረዳት አብራሪው ግን ጠላፊዎቹን “በቂ ነዳጅ የለንም ስለዚህ በአቅራቢያችን ባለ ቦታ አርፈን ነዳጅ መቅዳት አለብን” ቢሏቸውም ጠላፊዎቹ ግን አሻፈረኝ አሉ።

ከዚያም የአውሮፕላኖቹ ሁለቱም ሞተሮች አገልግሎት መስጠት አቆሙ።

አውሮፕላኑም ከፍታውን በከፍተኛ ፍጥነት በመቀነስ ወደታች መንደርደር ጀመረ።

በመጨረሻም በኮሞሮስ ደሴት አካባቢ ህንድ ውቅያኖስ ላይ ከውሃ ጋር ተላተመ፤ የአውሮፕላኑ ክፍሎችም በግፊቱ ብዙ ቦታ ተበታተኑ።

በአቅራቢያው የነበሩት የደሴቱ ነዋሪዎችና ጎብኚዎችም በፍጥነት ወደ አደጋው ቦታ በመሄድ የተረፉትንና የሞቱትን ሰዎች አስክሬን ከውሃ ውስጥ ማውጣት ችለዋል።

ዋና አብራሪው ካፒቴን ልዑል አባተ የጠላፊዎቹን ከፍተኛ የአካልና የአዕምሮ ጥቃት ተቋቁመው ውሃ ላይ ማሳረፍ በመቻላቸው በብዙ መገናኛ ብዙሃንና ከአደጋው በተረፉ ተጓዦች “ጀግና” በማለት ተወድሰዋል።

ዛሬ በናይሮቢ ኬንያ የሚኖሩት አቶ አስመላሽና ቤተሰባቸውም የሁለተኛውን የትውልድ ቀናቸውን 21ኛ ዓመት እያከበሩ ነው።

ስለአደጋው ማወቅ ያባችሁ ነገሮች

  • የአውሮፕላኑ ሞዴል ቦይንግ 767-260ER ሲሆን በአውሮፓውያኑ 1987 የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት ሆኗል
  • አብራሪዎቹ ዋና ካፒቴን ልዑል አባተና ረዳት አብራሪው ዮናስ መኩሪያ ነበሩ
  • አውሮፕላኑ 175 ተጓዦችንና የበረራ ቡድን አባላትን በመያዝ ወደ ናይሮቢ ለመጓዝ ነበር ከአዲሰ አበባ የተነሳው
  • አውሮፕላኑ ናይሮቢ የሚያደርሰውን ነዳጅ ብቻ ነበር ሞልቶ የተነሳው
  • በጉዞው መሃል 3 ሰዎች አውሮፕላኑን በመጥለፍ “አውስትራሊያ አድርሱን ካልሆነ ይህን ቦምብ እናፈነዳዋለን” አሏቸው
  • ወደ መጀመሪያ መዳረሻው ናይሮቢ የሁለት ሰዓት ተኩል ጉዞ ለማድረግ የተነሳው አውሮፕላን ከአራት ሰዓት በላይ አየር ላይ በመቆየቱ ነዳጁን ጨረሰ
  • በመጨረሻም በህንድ ውቅያኖስ በኮሞሮስ ደሴት ውሃ ላይ ተከሰከሰ
  • በአደጋው 125 ሰዎች ሲሞቱ ሁለቱን አብራሪዎችን ጨምሮ 50 ሰዎች ተርፈዋል

ሶስቱ ኢትዮጵያውያን ጠላፊዎችም ከሞቱት መካከል ናቸው።

ምንጭ: ቢቢሲ

Advertisement