ስለ ጠልሰም ወይም በተለምዶ የአስማት ጥበብ ተብሎ ስለሚጠራው ምን ያህል ያውቃሉ? – “Telsem” Or Magical Wisdom of Art

                                                     

ጠልሰም አስማታዊ ጥበብ ነው ፤ ትርጉሙ ደግሞ አምሳል፣ውክልና እንዲሁም ማስዋብ ማለት ነው።

ጠልሰም የተለየ ኀይል ያለው ጥበብ ነው።

ኢትዮጵያውያን ከሁለተኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ይሰሩት የነበረ ጥበብ መሆኑም ይነገራል።

ይህም ጥበብ በየገዳማቱ በብራናዎች ላይ አርፏል።

የጠልሰም ጥበብ ኃይል ያላቸውን ቃላት፣ዕፅዋት እንዲሁም ምልክቶችን ይይዛል።

ጠልሰም የመፈወስ ኃይል አለው ስለሚባል በክታብነት የሚጠቀሙበት አሉ።

ይህ ጥበብ በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ አካባቢዎች ብቻ ተወስኗል።

የጠልሰም ስዕልም እነዚህን ኃይል ያላቸውን ቃላቶች፣ ምልክቶችና ዕፅዋት በመጠቀም የሚሳል ነው።

ጠልሰም ከመፈወስ በተጨማሪ ሰውን የመሰወር፤ ግርማ ሞገስን መስጠት፤ በሰዎች ጫንቃ ላይ ለመስፈር የሚዳዳውን ሰይጣን ጋሻና ጦር በመሆን መከላከልና ማስጣል የሚያስችል ኃይል አለው ተብሎ ይታመናል፤ ይህም ዓቃቤ ርዕስ ተብሎ ይጠራል።

ለዛሬም ከአንድ ኢትዮጵያዊ ጠልሰምን የሚጠቀም ሰዓሊ እናስተዋውቃችሁ።

ተወልደብርሃን ኪዳነ አስመራ ከተማ ውስጥ ማይ ጃሕጃሕ በተባለ ልዩ ስፍራ ነው የተወለደው። የአንድ ዓመት ህፃን ልጅ ሆኖም ወደ ኢትዮጵያ መጣ።

በመቐለ የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተክርስትያን ውስጥ የአብነት ትምህርቱን የተማረው ከመርጌታ አርአያ ሲሆን በተጨማሪም ጥንታዊና እየጠፋ ያለውንም የጠልሰምን ዕውቀት አስተምረውታል።

የመደበኛ ትምህርቱን 8ኛ ክፍል ከደረሰ በኃላ ሁሉንም ነገር ጥሎ ወደ ጐጃም ጣና ቂርቆስ ገዳም ገባ።

ገዳሙ ውስጥ ለሦስት ዓመታት ያህል የጠልሰም ጥበብን ከሊቃውንት አባቶች ተማረ።

                                                         

የጠልሰምን ጥበብ ከአፈር፣ ከዕፅዋት፣ከቅጠልና ከአበባ እንዴት መሳል እንደሚቻልም ለዓመታት አጠና።

ወደ ሰሜን ወሎ በማቅናትም በአቡነ ይምርሃነ ክርስቶስ ገዳም ውስጥ ስለ ጠልሰም አንድ ዓመት ተምሯል።

ከዚያም በኃላ ሰሜን ሸዋ በሚገኘው የደብረ ሊባኖስ ገዳም በመሄድ የጠልሰምን ጥበብ ለአንድ ዓመት ተኩል ያህል አጥንቷል።

ተወልደብርሃን በዚህ አላበቃም ወደ ቢሾፍቱም በመሄድ በቤተ ሩፋኤል ገዳም ውስጥ አንድ ዓመት ከሦስት ወር በመቆየት በጠልሰም ዙሪያ ላይ ቁፋሮና ምርምር አካሂዷል።

ወጣቱ በነዚህ የምርምርና የጥናት ጊዜው ጠልሰም ትልቅ የኢትዮጵያውያን ስልጣኔ መሆኑን እንደተረዳ ይናገራል።

                                                             

“የመጀመርያው ሰዓሊ ራሱ ፈጣሪ ነው፤የሰው ልጅ የፈጣሪ የጠልሰም ጥበብ ውጤት ነው። የሰው ልጅም ከፈጣሪው የወረሰውን የጥበብ ኅይል ተጠቅሞ የጠልሰምን ጥበብ መከወን ችሏል። በዚሁ ዘዴ ከመላዕክት ጋር ይነጋገራል። ሲያሰኘው ደግሞ ጥበቡ እየረቀቀ በሄደ ቁጥር ከአጋንንት ጋርም ያወራል” በማለት ተወልደብርሃን ስለ ጠልሰም አፈጣጠርና መንፈሳዊ ግንኙነት ይገልፃል ።

በኢትዮጵያ የጠልሰም ጥበብና ሐረግ በየገዳማቱ ብራና ላይ ይገኛሉ። ተወልደብርሃን በጠልሰም ምርምር ዘልቆ የገባ ሲሆን የራሱን የፈጠራ ውጤት በማከል የተለያዩ ስዕሎችን ያዘጋጃል።

እስከ አሁን ድረስ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ሰዓሊያን ጋር በመሆን በአዲስ አበባ የአሜሪካ ኤምባሲ፣ብሔራዊ ቴአትር፣ነፃ አርት ቪሌጅ፣ሸራተን ሆቴል፣እንዲሁም በመቐለ ከተማ፣ በዓዲ ግራትና አክሱም ዩኒቨርሲቲዎች በተለያየ ጊዜ የጠልሰም ስዕሎች ዓውደ ርእይ አቅርቧል።

በመቶዎች የሚቆጠሩ የጠልሰም ስዕሎችንም ሰርቷል።

“ኢትዮጵያውያን ከጠልሰም በፊት የነበረውና ‘ርስተ ጌታ’ በሚል ይታወቅ የነበረው የጥበብ ጸጋ አጥተነዋል። ‘ርስተ ጌታ’ በስነ ፍጥረት ዙሪያ የሚያጠነጥን የስዕል ጥበብ ነበረ። በአሁኑ ሰዓት የዚህ ጥበብ አሻራ በደብረ ዳሞ ገዳም (ትግራይ) እንዲሁም በይምርሃነ ክርስቶስ ገዳም (ላልይበላ) ይገኛል” በማለት ተወልደብርሃን ይናገራል።

ይህንን ጥበብ ወደ ቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ዕቅድ ያለው ተወልደብርሃን ትግራይ ክልል ውስጥ ከክልሉ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር በአምስት አካባቢዎች በጠልሰም ጥበብ ዙሪያ ለወጣቶች ስልጠና ለመስጠት አቅዶ እንዳልተሳካለት ይናገራል።

“ጠልሰም ደግሞ ምንድን ነው? አሉኝ። ብራና ላይ ስዬ አሳየሁዋቸው፤ሊቀበሉት አልቻሉም፤ይኸው ቤቴን ዘግቼ እስላለሁ” ሲል ሁኔታው ምን ያህል እንዳልተመቻቸለት ገልጿል።

                                                      

ተወልደብርሃን ማታ እስከ እኩለ ሌሊት ሲስል ሻማ ማብራትና ዕጣን ማጨስ ይወዳል።

ባለፈው ዓመት ዘጠኙን ቅዱሳን ለመሳል 78 ሻማዎችን አብርቷል።

በኢትዮጵያ የጠልሰም ጥበብ ውስጥ ሴቶች አይሳተፉበትም ምክንያቱም ይህ ጥበብ የአስማት ነው ተብሎ ስለሚታወቅ ከባድ ተፅዕኖ ስለሚደርስባቸው ነው በማለት ተወልደብርሃን ይገልፃል።

ተወልደብርሃን በአሁኑ ሰዓት መቐለ በሚገኝ አንድ የሥነጥበብ ጥምህርት ቤት ዘመናዊ የስዕል ጥበብ ያስተምራል።

በቀጣይ አንድ ትልቅ የጠልሰም ጥበብ ውጤቶችን የሚያሳይ ዓውደ ርዕይ ለማዘጋጀት አቅዷል።

“ኢትዮጵያ ውስጥ ጠልሰም አደጋ ላይ ነው፤ሌላው ቀርቶ በውል ተጠንቶ አልተሰነደም። እኔ ያጠናሁትና የሰበሰብኩትን ዕውቀት በመፅሃፍ አሳትሜ ወደ ህዝቡ እንዳላቀርብ አጋዥ በማጣት ይኸው አቋረጥኩት” ሲል ተወልደ ብርሃን በምሬት ይናገራል።

ምንጭ: ቢቢሲ

Advertisement