እስራኤል ከ35 ሺ በላይ ስደተኞችን ልታባርር ነው – Israel is About to Expel More Than 35,000 Refugees

                                                    

ሰሞኑን የእስራኤል ባለስልጣናት ከ35ሺ በላይ ተቀማጭነታቸውን እስራኤል ያደረጉ የኤርትራና የሱዳን ስደተኞችን ወደ ሌላ ሃገር ለመዛወር ፍቃደኛ ካልሆኑ እስራት እንደሚጠብቃቸው ገልፀዋል።

ከተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን በተገኘው መረጃም 27500 ኤርትራውያንና 7800 ሱዳናውያን ስደተኞች ናቸው ከእስራኤል ወደ ሌላ ሀገር የሚዛወሩት።

የእስራኤል የሀገር ውስጥ ሚኒስትር አርየህ ዴሪ እና የህዝብ ደህንነት ሚኒስትር ጊላድ ኤርዳን ሰሞኑን ሀገሪቱ ውስጥ ያሉ ስደተኞችን በተመለከተ እስራኤል ያላትን ዕቅድ ይህ ይፋ የሆነው ነው።

ይህ እቅድ የጥገችነት ጥያቄ ያቀረቡ ስደተኞችንም እንደሚመለከት በቴልአቪቭ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ቢሮ የህዝብ መረጃና ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ ሻሮን ሐሬል ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ስደተኞችን ወደ ሶስተኛ ሃገር የማዛወሩ ጉዳይ ለኮሚሽኑ አሳሳቢም እንደሆነ ጨምረው ገልፀዋል።

እነዚህ ስደተኞች በህገ-ወጥ መንገድ ወደ እስራኤል እንደገቡ የሚናገሩት ሻሮን ብዙዎቹም ስደተኞች በግብፅ በኩል ድንበሩን አቋርጠው እንደገቡ ያስረዳሉ። “ብዙ ሴቶች እና ህጻናት መኖራቸው ችግሩን የተወሳሰበ ያደርገዋል” በማለት ሻሮን ይናገራሉ።

ይህ እቅድም ነሐሴ ላይ የእስራኤል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በአውሮፓውያኑ 2015 የእስራኤል መንግሥት አወዛጋቢ የሚባለውን ስደተኞችን በኃይል ወደ ሌላ ሀገር (ሶስተኛ ሃገር) ማዛወር ፓሊሲን መሻሩን ተከትሎ እንደሆነ ኮሚሽኑ በድረ-ገፁ አስታውቋል።

ሻሮን በበኩላቸው ስደተኞቹ በሚደርሱባቸው ሃገራት ደህንነታቸውና መብታቸው እንዲጠበቅ፤ የስራ ፈቃድም እንደሚያገኙ ከእስራኤል ባለስልጣናት በኩል ቃል ቢገባም እንዳልተተገበረ ይናገራሉ።

ፕሮግራሙ ከተተገበረበት ከአውሮፓውያኑ 2013 እስካሁን ባለው 4000 ኤርትራውያንና ሱዳናውያን ስደተኞች መንግሥት “ፈቃድ ያለው መዘዋወር ፕሮግራም” በሚል ወደ ሩዋንዳና ዩጋንዳ ልከዋል።

“የእስራኤል ባለስልጣናት እንደሚሉት ይህ በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ሳይሆን በሚስጥር እና ግልጽኘነት በልተሞላበት ሁኔታ የተፈጸመ ነበር” በማለት የሚናገሩት ሻሮን ሳይወዱ በግድ ከእስራኤል ወደ ሶስተኛ ሀገር ከተዘዋወሩ ስደተኞች ባገኙዋቸው የምስክርነት ቃል መረዳት ችለናል ብለዋል።

ከሩዋንዳ በህገ-ወጥ መንገድ ወደ ዩጋንዳ የተወሰዱ፤ ሃገራትን አቆራርጠው ወደ ኩባ የገቡ፤ ከኡጋንዳ ወደ ናይሮቢም በህገወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ ተገኝተው ለእስር የበቁም እንዳሉ ሻሮን ይናገራሉ።

“እነዚህ ስደተኞች በተዛወሩባቸው ሶስተኛ ሃገራት ደህንነት ስላልተሰማቸው ሜድትራንያን ባህርን በአደጋኛ ሁኔታ በማቋረጥ ወደ አውሮፓም ሊገቡ የሞከሩ ነበሩ” በማለት ሻሮን ተናግረዋል።

ይህንንም ሁኔታ ኮሚሽኑ በበላይነት መቆጣጠር እንዳልቻለም ይናገራሉ።

                                                                  

እአአ በ2014 በእስራኤል የሚኖሩ ስደተኞች ሀገሪቱ የጥገኝነት ጥያቄያቸውን እንድትቀበል ተቃውሞ ባካሄዱበት ወቅት።

እስካሁን ድረስ ብዙ ሺ ስደተኞች እስራኤል ቢደርሱም ለስምንት ኤርትራውያንና ለሁለት ሱዳናውያን ስደተኞችን ብቻ ባለስልጣናቶቹ እውቅና ሰጥተዋል።

በአጠቃላይ እስራኤል ውስጥ ያሉትን የስደተኞችን ሁኔታ የገመገሙት ሻሮን ስደተኞቹ የተለየ የመኖሪያ ፍቃድ ቢኖራቸውም በሃገሪቷ ውስጥ መስራት እንደማይችሉና አንዳንድ መብቶቻቸውም እንደተገደቡ ይናገራሉ።

“የመንቀሳቀስ መብት ያላቸው ቢኖሩም መብቶቻቸው ተገድበው በማቆያ ቤት ታስረው የሚኖሩ አሉ” በማለት ሻሮን ያለውን ሁኔታ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

እንደ እስር ቤት የሚታየው የስደተኞች ማቆያ ሆሎት ማዕከል እንዲዘጋ ሰሞኑን ካቢኔቱ አፅድቆታል። ይሄንንም በኃይል ስደተኞችን ወደ ሶስተኛ ሃገር የማዛወር ሁኔታም የእሰራኤል ፓርላማ የመጨረሻ ውሳኔ ሰሞኑን ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።

ኮሚሽኑ ያወጣውም መግለጫ እንደሚያትተው በአውሮፓውያኑ 1951 የተደረሰው የስደተኞች ስምምነት እስራኤል እነዚህን ስደተኞች ደህንነት ለመጠበቅ ህጋዊ ግዴታ እንዳለባት ነው።

መግለጫው ጨምሮም ኮሚሽኑም ሆነ አለም አቀፍ ማህበረሰቡ እስራኤል ግዴታዎቿን እንድትወጣ ድጋፍ ሰጥተዋታል። በባለፉት ዓመታትም ለ2400 የሚሆኑ ስደተኞችን ከእስራኤል ተቀብለው ወደሌላ ሃገር እንዲቆዩ አድርገዋቸዋል።

ምንጭ: ቢቢሲ

Advertisement