በሊቢያ ”የባሪያ ንግድ” እየተካሄደ እንደሆነ የሚያሳየው ተንቀሳቃሽ ምስል ድንጋጤን ፍጥሯል – Sale of African Migrants as Slaves in Libya

                                                                                                                                    

በሊቢያ አፍሪካዊያን ስደተኞች ለባሪያ ንግድ በጨረታ ሲቀርቡ የሚያሳይ ምስል ከወጣ በኋላ የአፍሪካ ሕብረት ድርጊቱ እጅጉን አስደንግጦኛል ብሏል።

ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ሲኤንኤን ይዞት የወጣው ቪዲዮ አፍሪካውያን ስደተኞች በጨረታ ለእርሻ ሥራ ሲሸጡ ያሳያል።

የአፍሪካ ሕብረት የወቅቱ ሊቀመንበር የጊኒው ፕሬዝዳንት አልፋ ኮንዴ ይህን ከዘመናት በፊት የተሻረውን አጸያፊ ተግባር የሚፈፅሙ መጠየቅ አለባቸው ብለዋል።

አውሮፓ ለመግባት ከሃገራቸው የሚወጡት አፍሪካውያን ስደተኞች በሕገወጥ አዘዋዋሪዎች በግድ ተይዘው አነስተኛ ገንዘብ ወይም ያለክፍያ የጉልበት ሥራ እንዲሰሩ ይገደዳሉ።

በሲኤንኤን ቪዲዮ ላይ ከኒጀር እና ከሰሃራ በታች ካሉ ሃገራት የመጡ ስደተኞችን ተጫራቾች እሰከ 300 የአሜሪካ ዶላር (8000 ብር ገደማ) ሲገዙ ያሳያል።

የሊቢያ መንግሥት ጉዳዩን ማጣራት እንደጀመረ ሲኤንኤን ዓርብ ዕለት ዘግቧል።

                                                         

በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ አፍሪካውያን ስደተኞች አውሮፓ ለመግባት ሜድትራንያን ባህርን ለማቋረጥ ይጥራሉ

ከዚህ በፊት ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት በሊቢያ የባሪያ ንግድ ስለመኖሩ መረጃዎችን አሰባስቢያለሁ ብሎ ነበር።

በሊቢያ የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ሃላፊ ኦትማን ቤልቢሲ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ስደተኞቹ የዋጋ ግምት የሚወጣላቸው እንደ ችሎታቸው መጠን ነው ይላሉ።

”ስደተኞቹ ወይም ቤተሰቦቻቸው ህግወጥ አዘዋዋሪዎቹ የሚጠይቁትን ገንዘብ መክፈል ስለማይችሉ በአነስተኛ ገንዘብ ይሸጣሉ” ብለዋል።

”ስደተኞቹ ከፍ ባለ ዋጋ ሊሸጡ የሚችሉት በሚኖራቸው ችሎታ ነው። ለምሳሌ ቀለም መቀባት የሚችል ወይም የግንባት ሥራ መስራት የሚችል ከሆነ ከፍ ባለ ዋጋ ሊሸጥ ይችላል” ሲሉ ኦትማን ያስረዳሉ።

ምንጭ: ቢቢሲ

Advertisement