ስለ ሆድ ድርቀት ምን ያህል ያውቃሉ? – Constipation

                                                                                        

አንድ ሰዉ ለተከታታይ ሳምንታትና ከዚያ በላይ በቂ ጊዜ ሰገራ መዉጣት የሚያስቸግረዉ ከሆነ ወይም በሳምንት ከሶስት ጊዜ በታች ሰገራ የሚወጣ ከሆነ ለረጅም ጊዜ የቆየ የሆድ ድርቀት( Chronic constipation) አለዉ ተብሎ ይገለፃል፡፡ጊዜያዊ የሆነ የሆድ ድርቀት ብዙ ጊዜ የሚከሰት ነገር ነዉ፡፡ ነገር ግን ለረጅም ጊዜ የቆየ የሆድ ድርቀት በሚከሰትበት ወቅት የታማሚዉን የዕለት ተዕለት የስራ እንቅስቃሴ ከማወኩም በላይ ታማሚዉ ሰገራ በሚወጣበት ወቅት ረዘም ላለ ጊዜ የማስማጥና ሌሎች ምልክቶችም አሉት፡፡

የሆድ ድርቀት ምልክቶች

• በሳምንት ከሶስት ጊዜ በታች ሰገራ መዉጣት

• የደረቀ ሰገራ መዉጣት

• ሰገራ በሚቀመጡበት ወቅት ማስማጥ

• ሰገራ በሚቀመጡበት ወቅት አንዳች ነገር ደንዳኔዎትን የዘጋዉ ነገር ያለ ስሜት መሰማት

ለሆድ ድርቀት የሚጋልጡ ነገሮች

• በእድሜ መግፋት

• ሴት መሆን

• በቂ ፈሳሽ ያለመዉሰድ

• በፋይበር( fiber) የበለፀጉ ምግቦችን ያለመጠቀም(አነስተኛ የፋይበር መጠን ያላቸዉን ምግቦች ማዘዉተር)

• አነስተኛ ወይም ምንም አይነት የአካል እንቅስቃሴ ያለማድረግ

• ለድርቀት ሊያጋልጡ የሚችሉ መድሃኒቶችን መጠቀም፡-ለምሳሌ የደም ግፊት ለመቀነስ የሚረዱ፣ለስነዓዕምሮ ችግሮች የሚሰጡ(ሴዳቲቭስና ናርኮቲክስ) የመሳሰሉት ናቸዉ፡፡

የሆድ ድርቀት መንስዔዎች

የሆድ ድርቀት አብዛኛዉን ጊዜ የሚከሰተዉ ከምግብ መፈጨት በኃላ የሚቀረዉ ቆሻሻ ወይም ሰገራ በአንጀት ዉስጥ የሚያደርገዉ እንቅስቃሴ(ጉዞ) በጣም ዘገምተኛ በሚሆንበት ወቅት ሲሆን የሚከተሉት መንስዔዎች አሉት፡-

ሀ. በትልቁ አንጀት ወይም በደንዳኔ ዉስጥ መዘጋት በሚኖርበት ወቅት

ለ. በትልቁ አንጀትና በደንዳኔ አካባቢ ባሉ ነርቮች ላይ ችግር በሚከሰትበት ወቅት

የነርቭ ችግር መኖር በዳንዳኔና ትልቁ አንጀት ጡንቻዎች ላይ መኮማተርን ስለሚያስከስት የሰገራን እንቅስቃሴ ይገድባል፡፡

ሐ. ሰገራን ከሰዉነት ለማስወገድ በሚረዱ ጡንቻዎች ላይ ችግር መከሰት

መ. በሰዉነት ዉስጥ ባሉ ሆርሞኖች ላይ ችግር መከሰት

ሆርሞኖች በሰዉነታችን ዉስጥ ያለዉ ፈሳሽ ተመጣጥኖ እንዲገኝ የሚያደርጉ ሲሆን ይህንን ስርዓት የሚያዛቡ ህመሞች ካሉ ለሆድ ድርቀት ሊያጋልጡ ይችላሉ፡፡

ምንጭ:- ዶክተር አለ(Doctor Alle)

Advertisement