ከማደጎ ልጅነት ወደ እውቅ ገጣሚና የማንችስተር ዩኒቨርሲቲ ሃላፊነት

ነጮቹ ለምን ሲሴ እይሉ ይጠሩታል። በ1950ዎቹ መጨረሻ ላይ ለትምህርት ወደ እንግሊዝ ሃገር የሄደችው የማርእሸት ያልፈቀደችውን ልጅ ታረግዛለች። ልጅ ወልዶ ለማሳደግ ዝግጁ ስላልነበረች የወለደችውን ልጅ ‘ለምን’ ብላ ሰየመችው። ከዚያም ለምን ሲሳይ በሁለት ወሩ ለማደጎ ተሰጠ።

                                                           

ከወራት በኋላ የማርእሸት ልጇን ማሳደግ የምትችልበት ደረጃ ላይ ስትደርስ ልጄን መልሱ ብላ አቤቱታ አቀረበች። የማህበራዊ አገልግሎቱ ግን ፍቃደኛ ሳይሆን ቀረ።

ኖርማን የተባለው የማህበራዊ አገልግሎት ሰራተኛ ስሙን ከ ‘ለምን’ ወደ ራሱ ስም ‘ኖርማን’ ቀየረው። ከዚያም ለነጭ አሳዳጊዎች በማደጎነት ሰጠው።

ወግ አጥባቂ የነበሩት የማደጎ ወላጆቹ በሙያቸው መምህር እና ነርስ ነበሩ። ለምን የልጅነት ጊዜውን ”አስከፊ” ሲል ይገልፀዋል። በእድሜ ከፍ እያለ ሲመጣ ለአሳዳጊዎቹ ”አስቸጋሪ” ልጅ ሆነ።

ምግብ የመብላት ፍላጎት የለውም፣ ወደ ቤት መግባት አይፈልግም፣ በአጠቃላይ በህይወቱ ደስተኛ አልነበረም። 12 ዓመት ሲሞላው አሳዳጊዎቹ ዳግመኛ ልናየው ፍቃደኛ አይደለንም ብለው ለማህበራዊ አገልግሎት ሰራተኞች መልሰው ሰጡት።

አስራ ስምንት ዓመት እስኪሆነው ድረስ በአራት የህፃናት ማሳደጊያ ቤቶች ውስጥ ኖሯል። በእነዚያ ዓመታትም በዘር ላይ የተመሰረቱ አካላዊና ሥነ-ልቦናዊ ጥቃቶች ተፈፅመውበታል። ወላጅ እናቱም ጥላው እንደሄደች፤ ወገን እንደሌለው ይነገረው ነበር።

አስራ ስምንት ዓመት ከሆነው በኋላ ስለ እራሱ እና ወላጅ እናቱ የሚያትቱ ጥቂት መረጃዎች ተሰጥተውት ከማደጎ አንዲወጣ ተደረገ። በዚያን ወቅት ነበር ወላጅ እናቱ ”ለምን” ብላ እንደሰየመችው እና የማህበራዊ አገልግሎት ሰራተኛው ሰሙን ወደ ኖርማን እንደቀየረ የተረዳው።

እናቱም ለማህበራዊ አገልግሎት ልጇ እንዲመለስላት በፃፈችው ደብዳቤ ”ለምንን እንዴት መልሼ ማግኘት እችላለሁ? ከራሱ ሰዎች ጋር እንዲሆን እፈልጋለሁ፤ አድልዎ እንዲፈፀምበት አልፈልግም” ስትል እንደተማፀነች የተረዳው። ብዙም ሳይቆይ መጠሪያ ስሙን ከኖርማን ወደ ለምን አሰቀየረ።

ለምን ከማደጎ ቤት ከወጣ በኋላ የብቸኝነት ስሜት እጅጉን ይሰማው እንደነበር ይናገራል። ”በበዓላት ወቅት የቤተሰብ አባላት በአንድ ላይ ተሰብሰበው ሲያከብሩ እኔ ግን ብቸኛ ነበርኩ። ለዚያም ነው አሁን በተቻለኝ አቅም በማደጎ ቤት ውስጥ ያሉ ልጆችን በቤቴ ሰብስቤ በገና ዋዜማ እራት የምጋብዛቸው” ሲል ይናገራል።

                                               

ለምን ከማደጎ ቤት ከወጣ በኋላ ማንችስተር ከተማ በሚገኝ ማተሚያ ቤት ውስጥ የሥነ-ፀሑፍ ሥራውን እየሰራ ወላጅ እናቱን ማፈላለግ ጀመረ።

ወላጅ እናቱን ለበርካታ ዓመታት ካፈላለጋት በኋላ፤ 21 ዓመት ሲሆነው ጋምቢያ ውስጥ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እየሰራች የነበረችውን የማርእሸትን አገኛት።

ለምን ስለ ወላጅ እናቱ ሲናገር ”የእናቴ ፎቶግራፍ የተሰጠኝ ከተማረችበት ኮሌጅ ሲሆን፤ እናቴን ለመጀመሪያ ጊዜ ሳገኛት 21 ዓመቴ ነበር። ይህም እሷ አባቴን ያገኘችበት እድሜ ማለት ነው። እናቴ እና አባቴ ለመጀመሪያና ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኙት እኔ በተፀነስኩበት ምሽት ነበር።” የሚለው ለምን ”የማርእሸት ሲሳይ አስደናቂ ሴት ናት። ካወራን ከዓመት በላይ ቢሆንም ብዙ ጊዜ ተገናኝተናል” ሲል ያስታውሳል።

ዛሬ ላይ ለምን የበርካታ ተወዳጅ መፅህፍት፣ የተውኔት ድርሰቶች እና የግጥሞች ፀሃፊ ነው። ከዚህ በተጨማሪም የማንችስተር ዩኒቨርሲቲ ቻንስለር ሲሆን ከሁለት የእንግሊዝ ሃገር ዩኒቨርሲቲዎች የክብር ዶክትሬቶችን ተቀብሏል።

ምንጭ: ቢቢሲ

Advertisement