የሐረማያ ሃይቅ ሕይወታችን ነበር። አሁን ግን እሱም የለም – Haramaya Lake

                                                             

የሐረማያ ሃይቅ ከደረቀ በኋላ የአካባቢው አርሶ አደሮች ኑሮ እጅግ መራራ ሆኗል።

ከዓመታት በፊት ሐረማያ ሃይቅን በጀልባ እንዳላቋረጡ፣ ዓሳ እንዳላጠመዱበት እና በመስኖ ሰብል እንዳላበቀሉበት ዛሬ ላይ ኑሯችን በሃይቁ መድረቅ ምክንያት ከባድ ሆናብናለች ይላሉ የአካባቢው ነዋሪዎች።

የተለያዩ ሰብሎችና እንዲሁም ጫት በብዛት ተመርቶ ወደ አቶ በድሪ ዩሱፍ ቤት መግባት ካቆመ በርካታ ዓመታት ተቆጥረዋል።

በአካባቢው ተወልዶ ያደገው ወጣት ነጃሻም ”ይህ ሃይቅ የሐረማያ ሕይወት እና ጤና ነበር። ለአካባቢው ነዋሪዎችም ትልቅ ሃብት ነበር። ዛሬ ላይ ግን ሃይቁ በመድረቁ የአካባቢው አርሶ አደሮች ኑሯቸውን ለመግፋት የሚያስችል ምርት እያመረቱ አይደሉም። እጅግ በጣም አሳሳቢ ችግር ውስጥ ነን” ሲል ይናገራል።

የሰው ልጅ እጅ እና የአየር ንብረት ለውጥ

የሐረር ከተማ ዛሬም ድረስ ነዋሪዎቿን ከሐረማያ ሃይቅ ስር የሚፈልቀውን ውሃ ታጠጣለች።

የሐረር ቢራ ፋብሪካ ቢራ አምርቶ የሚሸጠው የሃይቁን የከርሰ ምድር ውሃ በመጠቀም ነው። የሐረማያ ዩኒቨርሲቲም ቢሆን የውሃ ፍላጎቱን የሚያረካው ከሃይቁ ነው።

ከአስር ሺህ በላይ የሚሆኑ የውሃ መሳቢያ ፓምፖች የአካባቢውን አርሶ አደር እርሻ ለማጠጣት ውሃ ሲመጡ ይውሉ ነበር።

ልክ ያለፈው የውሃ አጠቃቀም ጉድለት እና የአየር ንብረት ለውጥ የሃረማያ ሃይቅን አቅም አዳክመውታል።

በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የሐረማያ ሃይቅ ተፋስስ የቴክኒክ አስተባባሪ የሆኑት አቶ ተፈሪ ታደሰ ”የውሃ አጠቃቀም ሕግ ባለመኖሩ የውሃ አካሉ መስጠት ከሚችለው በላይ ግልጋሎት ሰጥቷል። በሃይቁ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ነው የደረሰው፤ የከተማው የውሃ በጀትንም ከዜሮ በታች አድርጎታል” ሲሉ ያብራራሉ።

የሐረር ከተማ አስተዳደር እና የሐረር ቢራ ፋብሪካ እንዲሁም የአወዳይ ከተማ ሃይቁን ወደ ቀድሞ ቦታው ለመመለስ በሚደረገው ጥረት ምንም ዓይነት ተሳትፎ እያደረጉ እንዳልሆነ ከሐረማያ ዩኒቨርሲቲ እና ከሐረማያ ከተማ አስተዳደር ሰምተናል።

የሐረማያ ሃይቅ መልሶ እንዲያገግም በ15 ሺ ሄክታር ላይ የተፋሰስ ሥራ መሰራት ቢኖርበትም እየተሰራ ያለው ግን እጅግ አነስተኛ በሆነ ቦታ ላይ እንደሆነም ማወቅ ችለናል።

በሃይቁ ላይ በሶስት ቡድን እየሰራ የሚገኘው የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ”የገንዘብ እጥረት የሐረማያ ሃይቅን መልሶ ለማምጣት በማደርገው ጥረት ፈተና ሆኖብኛል” ሲል ያማርራል።

13 ዓመታት በርካታ ችግሮች

”ከ13 ዓመታት ወዲህ ከአቅማችን በላይ የሆኑ ችግሮችን እየተጋፈጥን ነው። ሃይቁ ከደረቀ በኋላ ድንችም ሆነ ጫት ማምረት አልቻልንም። በዚህም በጣም ተገጎድተናል” በማለት የአካባቢው ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ ፋጤ ይናገራሉ።

የአካባቢው አርሶ አደሮች ሐረማያ ሃይቅ ሰብሎቻቸውን ከውርጭ ይከላከል እንደነበረ አሁን ግን ሃይቁ በመድረቁ ተክሎች በውርጭ ምክንያት ሰብል ላይ ጉዳት እየደረሰ እንደሆነ ይናገራሉ።

ከዚህ በተጨማሪም የአካባቢው ነዋሪ የመጠጥ ውሃ እጥረት እንዳለበት ቢቢሲ መመልከት ችሏል።

የሐረማያ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አብዲ አህመድ ”ሐረር ቢራ ፋብሪካ ለቢራ ማምረቻ ከሚያመነጨው ውሃ በተዛማጅ ለአካባቢው ህዝብም የመጠጥ ውሃ ለማዳረስ በመርህ ደረጃ ተስማምቷል” በማለት ለቢቢሰ ተናግረዋል።

በአሁኑ ስዓት ሃይቁን ወደነበረበት ለመመለስ የሚሰራው ስራ በቂ አለመሆኑን አቶ ተፈሪ ይናገራሉ። አቶ አብዲ ደግሞ የፌደራል መንግሥት ምንም አይነት ድጋፍ እያደረገልን አይደለም ይላሉ።

አስቸኳይና መጠነ ሰፊ የሆነ የተፋሰስ ስራ ካልተሰራ፣ የሃይቁ ውሃ አጠቃቀም ሥርዓት ካልተበጀለትና ሁሉም ሃላፊነቱን ከልተወጣ ችግሩ ከአካባቢው አልፎ በዙሪያው የሚገኙ ከተሞችና ተቋማት ላይ የከፍ ችግር ያደርሳል ሲሉ አቶ ተፈሪ ያስጠነቅቃሉ።

 

ምንጭ: ቢቢሲ

 

Advertisement