አይሲስ ሞሱል ውስጥ 741 ሰላማዊ ሰዎች መግደሉ ተነገረ – ISIS Killed 741 Civilians During Mosul Battle

                                             

የኢራቋን ከተማ ሞሱልን ለማስለቀቅ በተካሄደው ዘመቻ ወቅት ቢያነስ 741 ሰላማዊ ሰዎች በአይ ኤስ ታጣቂዎች ሆን ተብሎ እንደተገደሉ የተባበሩት መንግሥታት ድረጅት ገለፀ።

እስላማዊ ቡድኑ የጅምላ እገታ፣ ሰዎችን ከጥቃት መከለያ ማድረግና፣ የመኖሪያ አካባቢዎችን ሆን ብሎ በከባድ መሳሪያ መደብደብ እና እየሸሹ ያሉ ሰዎችን ኢላማ ያደርግ እንደነበር ተገልጿል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ተጠሪ የሆኑት ዛይድ ራድ አልሁሴን ”የዚህ አስከፊ ወንጀል ፈፃሚዎች ተጠያቂ መሆን አለባቸው” ብለዋል።

ተጠሪው በተጨማሪም በኢራቅ መንግሥት ኃይሎች ተፈፅመዋል በተባሉት የመብት ጥሰቶች ላይ ምርመራ እንዲደረግ ጠይቀዋል።

የተባበሩት መንግሥታት እንዳለው ሌሎች 461 ሰላማዊ ሰዎች የኢራቅና የአሜሪካ ጥምር ኃይሎች በዘመቻው ወቅት ባካሄዷቸው የአየር ድብደባዎች ምክንያት ተገድለዋል።

ሃሙስ የወጣው የመንግሥታቱ ድርጅት ሪፖርት እንዳሰፈረው በአብዛኛው በአይ ኤስ በተፈፀሙ ጥቃቶች በአጠቃላይ ቢያንስ 2521 ሰላማዊ ዜጎች ሲገደሉ ሌሎች 1673 የሚሆኑት ደግሞ በወታደራዊ ዘመቻው ወቅት ቆስለዋል።

ሪፖርቱ እንዳለው ባለፈው ዓመት የአይ ኤስ አባላት በቡድኑ ቁጥጥር ስር በነበሩ የሞሱል ክፍሎች ውስጥ እየተዘዋወሩ በድምፅ ማጉያ እንዳሳወቁት፤ በኢራቅ መንግሥት ኃይሎች እጅ ውስጥ የገቡት አካባቢዎች ነዋሪዎች ወታደሮቹ ከተማዋን እንዳይዙ ባለመዋጋታቸው እነሱም ኢላማ እንደሚሆኑ ተናግረው ነበር።

ከተማዋን ለመያዝ በተደረገው ዘመቻው ወቅት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ዓለም አቀፍ ህጎችን በሚጥስ ሁኔታ አስደንጋጭ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንደተፀመባቸው ተጠሪው ተናግረዋል።

”በየትኛውም ጦርነት ወቅት ሆን ተብሎ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈፀሙ ግድያዎች፣ በቤተሰብ ላይ የተፈፀሙ ሰቆቃዎች እና በንብረት ላይ የተፈፀሙ ውድመቶች ይቅር የማይባሉ ድርጊቶች በመሆናቸው ፈፃሚዎቹ ለጭካኔ ድርጊታቸው መጠየቅ ይኖርባቸዋል” ሲሉ ዛይድ ተናግረዋል።

ሪፖርቱ ጨምሮም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በዘር ማትፋት፣ በሰብአዊ ፍጡር ላይ በሚፈፀም ወንጀልና የጦር ወንጀል ፈፃሚዎች ተጠያቂ እንዲሆኑ እርምጃ እንዲወስድ ጥሪ አቅርቧል።

የኢራቅ ፍርድ ቤቶች ዓለም አቀፍ ወንጀሎችን የመመልከት ሥልጣን ስለሌለው እና አቃቤ ሕጉም ወንጀሎቹን ለመመርመር አቅሙ ስለማይኖረው የሃገሪቱ መንግሥት የዓለም አቀፉን የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ሥልጣን እንዲቀበልም ጠይቋል።

ምንጭ: ቢቢሲ

 

Advertisement