ተዓምራዊቷ ቅድስት ማርያም ውቕሮ ገዳም – The Mysterious St. Mary Monastery in Ethiopia

ትግራይ ምድር አቅፎ ከያዛችው ከ120 በላይ የሆኑት ከአለት ተፈልፍለው የታነፁት አብያተ ክርስትያን ለዛሬ አንዱን እናስተዋውቃችሁ።

ቅድስት ማርያም ውቕሮ ትባላለች። ወደ አካባቢው ለመድረስ በጣም አስቸጋሪ የጠጠር መንገድና ወንዝ መሻገር የግድ ነው። መኪናችን ወንዙን መሻገር አቅቷት ስትንገዳገድ የተመለከቱት የአከባቢው አርሶ አደሮች ተጠራርተው መንገዱን አስተካክለው አሻግረውናል።

ወደ ገዳሙ ቅጥር ግቢ ከተገባ በኋላ መጀመርያ ከአለት የተሰራው ሙዳዬ ምጽዋት ይገኛል። የገዳሙ አስተዳዳሪ ቄስ ዘሚካኤል ወልደጊዮርጊስ ሙዳዬ ምጽዋቱን ከማለፋችን በፊት ጫማችንን እንድናወልቅ ቀጭን ትዕዛዝ አስተላለፉ።

በሰንሰለት ዙርያ ጥምጥም የተቆለፈው የገዳሙን በር ከፍተው አስገቡን። የበሩ መዝጊያ ከአንድ የዛፍ እንጨት ብቻ እንደተዘጋጀ ለመረዳት አይከብድም።

ቄስ ዘሚካኤል፤ ገዳሟ መቼና እንዴት እንደተቆረቆረች ይናገራሉ።

“ይህች ገዳም ንግሥት ማርያም በ333 ጐንደር ላይ ሆነው በህልም ተገልፆላቸው ነበር የታነፀው። ደግሞ የሰው ልጅ በዶማ ቆፍሮ ነው ያነፀው በሉና እመኑ” ሲሉ አፌዙብን። ብታምኑም ባታምኑም ‘አብ ሃነጸ ወልድ መንፈስ ቅዱስ’ ራሱ መንፈስ ቅዱስ ነው ያነፃት ብለን ነው የምናምነው” ይላሉ።

ገዳሟ ውስጥ የአንድ ትልቅ የጥድ ዛፍ ቁመት ያላቸው 44 ዓምዶች ይገኛሉ። በሌሎች ገዳማትና አድባራት እንደሚደረገው ሁሉ በቅድስት ማርያምም ወንዶችና ሴቶች ተለያይተው ነው የሚቀመጡት።

በጣሪያው ላይ ሦስት እምነ አድማስ ነበሩ። አንደኛው ወድቆ እንድያውም ጣልያን ለመውሰድ ሞክሮ አልተሳካለትም። ሁለቱ እስከ አሁን ድረስ አሉ። ድንጋዩ ላይ በእብራይስጥ ቋንቋ የተፃፈ ፅሑፍም ይታያል።

እምነ አድማስ ድንጋይን ለመቁረጥና ለመጥረብ ኃይል የተሰጠው የድንጋይ ዘር ነው።

ገዳሟ ውስጥ ከሚታወቅ ይልቅ የማይታወቀው ስለሚበዛ ቄስ ዘሚካኤል ያስታወሱትንና የነገሩንን ብቻ አሳጥሬ ልንገራችሁ።

በአንድ የገዳሟ ጓዳ ውስጥ ልጅ መውለድ የዘገየባችው እንስቶች ተቀምጠው ፈጣርያቸውን የሚለምኑበት ከአለቱ ተፈልፍሎ የተዘጋጀ ወንበር ይታያል። ከፊት ለፊቱ ደግሞ መባ የሚያስቅምጡበት መደርደርያ አለ። 

በአንደኛው የገዳሟ ክፍል የቅድስት ማርያም መንበረ ታቦት አለ። መንበረ ታቦቱ ራሱ ሙሉ ለሙሉ ከአለት ተፈልፍሎ ነው የተሰራው።

ከመንበረ ታቦቱ አናት ላይ 4 ጉልላት ይታያል። ወደ መንበረ ታቦቱ ከካህንና ከዲያቆን ውጪ ምዕመን እንዲገባ አይፈቀድለትም።

ገዳሟ ውስጥ የሚገኘው የጨለመው በር ፈለገ ኦር ይባላል። ሊቃውንቱ ጉድጓዱ ቀጥ አድርጐ እስራኤል ነው የሚያስገባው ብለው ያምናሉ። ድሮ ነው አሉ 5 ካህናት ማሾና ጧፍ ይዘው ገብተው በዛው አልተመለሱም ብለውናል።

መሪጌታ ቁጭ ብሎ ወደ ታቦቱ እያየ የሚጸልይበት ዙፋንም ተቀርጾ ይታያል። ዙፋኑ ከላይ ዘውድ አለበት፤ ይህም ከአለት ተፈልፍሎ ነው የተዘጋጀው።

ገዳሟ ውስጥ የተለያየ ትርጉም ሊሰጣቸው የሚገቡ 5 ጉልላት አሉ፤ የኮከቦች ተምሳሌት ብለው የሚጠሩዋቸው ቅርፆችም አሉ።

የገዳሟ የበር መዝጊያዎች ከእየሩሳሌም በቀስተ ደመና ተጠፍረው እንደመጡ ይነገራል። ገዳሟ በር የሌላቸው 12 መስኮቶችም አሉት።

ልክ እንደ መንበረ ታቦቱ ከካህንና ዲያቆን ውጪ ሌላው ምዕመን የማይገባበት ቤተልሔምም አለ።

በአንድ ትልቅ አለት ላይ ሆኖ ከቅድስት ማርያም በተጨማሪ የቅዱስ ጊዮርጊስ ገዳም አለ። ገዳሟ መወጣጫ አልነበራትም። በቅርቡ አንድ ምግባረ ሰናይ ግለሰብ ከብረት የተዘጋጀ መሰላል አሰርቶላታል። 

 ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ገዳም የሚያስወጣ መሰላል

የቅዱስ ጊዮርጊስ ገዳም መስኮተ አብርሃምን ጨምሮ 6 መስኮቶች አሉዋት። በመስኮተ አብርሃም በኩል አሻግሮ የቅድስት ማሪያም መንበረ ታቦትን ማየት ይቻላል።

ሁለቱ ገዳማት ተአምራዊ የጥበብ ሥራ እንዳረፈባቸው ፍንትው ብሎ ይታያል።

እነኝህን ታሪካዊ ገዳማት በእንግዶች እንዳይጐበኙ ወደ አከባቢው የሚወስደው የመኪና መንገድ አይመችም። ሌላው ቀርቶ ወንዙን በቀላሉ ለመሻገር እንኳን ድልድይ አልተሰራለትም። የወረዳው አስተዳደር ድልድዩን ለመስራት ሽርጉድ ሲል ተመልክተናል።

ትግራይ ምድር ውስጥ የሚገኙት አብዛሃኛዎቹ ገዳማት በየተራራውና ሸንተረሩ ስለሚገኙ መሰረተ ልማት ካልተሟላላቸው በእንግዶች ሊጐበኙ አይችሉም።

መንግሥት በዚህ ዙርያ ብዙ መስራት ይጠበቅበታል። ሌላው ቀርቶ ገዳማቱን ለማየት የሚሄዱት እንግዶች የሚያርፉበት መጠለያ እንኳን የላቸውም። ባለሃብቶችም መዋዕለ ንዋያቸውን በዚሁ ዙርያ እንድያውሉ ማበረታትና ሁኔታውን ማመቻቸት ይጠበቃል።

ገደማቱም ጥገናና እንክብካቤ ይሻሉ። ከዚህ ውጭ የቅድስት ማሪያም ውቕሮ ተአምራዊ ናት ከማለት ባለፈ የተሰነደ ማስረጃ እንኳን የላትም።

ምንጭ: ቢቢሲ

Advertisement