የሳዑዲ ሮቦት ከሴቶች በላይ ዜግነታዊ መብት ይኖራት ይሆን? – Does Saudi Robot Citizen Have More Rights Than Women?

          

ሮቦቷ ሶፊያን ተዋወቁዋት ለመጀመሪያ ጊዜ ሰኞ ቀን በሳዑዲ አረቢያዋ ከተማ ሪያድ በአደባባይ ላይ ታይታለች።

በአጭር ጊዜ ታዋቂነትን ማትረፍ የቻለችው ሶፊያ ታሪካዊ በሚባል ሁኔታ ከሁለት ቀናት በፊት የሳዑዲ ዜግነት ተሰጥቷታል፤ ይህም የሆነው ከመቶዎች በላይ ልዑካን በተገኙበት ፊውቸር ኢንቨስትመንት ኢንሺየቲቭ ስብሰባ ላይ ነው።

የሶፊያ ፎቶዎችና ቪዲዮዎች በተለያዩ ድረ-ገፆች በወጡበት ወቅት በብዙዎች ዘንድ እንዴት ነው አንዲት ሮቦት ከሴቶች በላይ የበለጠ መብት ማግኘት የቻለችው የሚል ጥያቄን አጭሯል።

“በዚህ ታሪካዊ ቀን በዓለም የመጀመሪያዋ ሮቦት የዜግነት ዕውቅና ተሰጥቷታል። እባካችሁ አዲሷን የሳዑዲ ዜጋን ሶፊያን እንቀበላት”የሚል ንግግር በስብሰባውም ተሰምቷል።

ሶፊያን የፈጠራት ሃንሰን ሮቦቲክስ የሚባል የሆንግ ኮንግ ኩባንያ ነው።

በስብሰባውም ወቅት የሳዑዲ ሴቶች ግዴታ የሆነባቸውን አባያ ሳትለብስ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ንግግር አድርጋለች።

“ለዚህ ለየት ላለ ማዕረግ በመብቃቴ ክብር ተሰምቶኛል። ሮቦት የዜግነት ዕውቅና ስታገኝ የመጀመሪያዋ መሆኑም ታሪካዊ ያደርገዋል” ብላለች

ሳዑዲዎች ይህንን ዜና በተቀላቀለ መልኩ ሲሆን የተቀበሉት የሳዑዲ ዜግነት ያገኘች ሮቦት በሚል መልዕክትም ዜናው ከተሰማበት 24 ሰዓት ውስጥ ከ30 ሺዎች በላይ በተለያዩ ማህበራዊ ድረ-ገፅ አጋርተውታል።

በተቃራኒው ጉዳዩን በስላቅ የወሰዱትም አሉ።

ሶፊያ ጠባቂ አትፈልግም በሚል መልዕክት ከ10 ሺዎች በላይ በተለያዩ ማህበራዊ ድረ-ገፅ ፅፈዋል።

በሳዑዲ ስርአት መሰረት አንዲት ሴት ብቻዋን መንቀሳቀስ የማይፈቀድላት ሲሆን፤ ከቅርብ ቤተሰብ ወይም አንድ ወንድ ጠባቂ ያስፈልጋታል ይላል።

“ሶፊያ ጠባቂ የላትም፤ ፊቷን አትሸፋፈንም ። ለምን ይሆን?” በሚል ጥያቄ ትዊተር ድረ-ገፅ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ አልታጡም

ሌላኛው አስተያት ሰጪ ደግሞ ሶፊያን ጥቁር ቡርቃ ካለበሳት በኋላ፤ ሶፊያ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ይህንን ነው የምትመስለው ብሏል።

ሶፊያን ከሳዑዲ ሴቶች ከማወዳደር በተጨማሪ ዜግነት ያገኘችበት ቅለትና ፍጥነት የመወያያ ርዕስ ሆኗል።

“ይህቺ ሮቦት ሙሉ ህይወታቸውን በስደተኝነት ከሚሰሩ ሰዎች በፊት ዜግነት ማግኘት ችላለች” በማለትሙርታዛ ሑሴን የተባለች ጋዜጠኛ አስተያየቷን ሰጥታለች።

በሳዑዲ ህግ መሰረት ከውጭ አገራት የመጡ ሰራተኞች ያለ አሰሪዎቻቸው ፍቃድ መንቀሳቀስ አይችሉም፤ ይህም ሁኔታ መብታቸውን ገድቦታል።

በገልፍ አካባቢ ያሉ ግዛቶች ከመቶ ሺዎች በላይ ከውጭ አገር የመጡ የቤት ሰራተኞች ጥገኛ ናቸው።

“ሰው መሰል ሮቦቷ ሶፊያ የሳዑዲ ዜግነት ማግኘት ችላለች፤ በተቃራኒው ግን መሄጃ የሌላቸው ሀገር የለሽ ሚሊዮኖች አሉ” በማለት የሊባኖስ -እንግሊዛዊ ጋዜጠኛ ካሪም ቻሐይብ የተናገረ ሲሆን “መኖር ደጉ ስንቱን ያሳየናል”ብሏል።

ሳዑዲ አረቢያ በገልፍ ግዛቶች ላይ ያሉ ህግጋቶችን በማሻሻል ላይ ናት።

ሴቶች በሳዑዲ አረቢያ ሀገራዊ ቀን ላይ እንዲሳተፉ እንዲሁም ማሽከርከር ላይ ተጥሎ የነበረውም ዕገዳ ከወር በፊት ተነስቷል።

ከዚህም በተጨማሪ በነዳጅ ላይ ብቻ ጥገና የነበረውን የግዛቷን ኢኮኖሚም ለማስፋፋትም በልዑል ሞሐመድ ቢን ሳልማን ‘ራዕይ 2030’ በሚልም ዕቅድ ተይዟል። 

ምንጭ:- ቢቢሲ

 

Advertisement