በዩኒቨርሲቲው ኢንጅነሪንግ ትምህርት ክፍል ብንመደብም በሌላ የትምህርት መስክ እንድንማር ተደርገናል – ተማሪዎች – Chose to study Engineering

                                                     

በተመስገን እንዳለ

ትምህርት ሚኒስቴር በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኢንጅነሪንግ ትምህርት ክፍል ቢመድበንም ዩኒቨርሲቲው ከህግ ውጪ በሌላ የትምህርት መስክ መድቦናል ሲሉ ተማሪዎች ቅሬታ አቀረቡ።

ተማሪዎቹ ለከፍተኛ ትምህርት ተቋም ምደባ የሚያበቃቸውን ውጤት በማምጣት፥ በሀገር አቀፍ ትምህርት ምዘና እና ፈተናዎቸ ኤጀንሲ ለ2010 የትምህርት ዘመን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢንጅነሪንግ ሳይንስ ትምህርት ዘርፍ መመደባቸውን ይናገራሉ።

ይሁንና የተመደብንበት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሰቲ ትምህርት ሚኒስቴር በምደባ ካሳወቀን የትምህርት መስክ ውጭ፥ መድቦናል ሲሉ ነው ቅሬታቸውን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያቀረቡት።

እንዲህ ያለው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምደባ ሂደት ህግን ያልተከለለ ነው የሚሉት ተማሪዎቹ በተደጋጋሚ የተቋሙን የስራ ሃላፊዎች ቢያናግሩም ተገቢ ምላሽ አለማግኘታቸውን ይገልጻሉ።

ከተማሪዎቹ ከቀረበው ሰነድ መረዳት እንደቻልነውም ተማሪዎቹ በትምህርት ሚኒስቴር የተመደቡበት የትምህርት መስክ እና የዩኒቨርሲቲው ምድባ የተለያየ ነው።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ሬጅስትራር ሃላፊ አቶ መሰለ ብርሃኑ ደግሞ፥ ዩኒቨርሲቲዉ በኢንጅነሪንግ ዘርፍ ከትምህርት ሚኒስቴር 700 ተማሪዎችን ለመቀበል አመልክቶ ከ900 በላይ ተማሪዎችን እንዲቀበል መደረጉን ያነሳሉ።

በዚህ ሳቢያም ተቋሙ ካመለከተው ውጭ ያሉትን ተማሪዎች በሌላ የትምህርት መስክ ለመመደብ ተገዷል ብለዋል ምክትል ሬጅስትራር ሃላፊው።

ዩኒቨርሲቲው ለትምህርት ሚኒስቴር የኮምፒውተር ሳይንስ ተማሪዎችን ለመቀበል ጥያቄ ማቅረቡን ያስታወሱት ምክትል ሬጅስትራር ሃላፊው፥ በሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች ኤጀንሲ በኩል ግን የተማሪዎች ምደባ አለመደረጉን ተናግረዋል።

በዚህ ምክንያትም ዩኒቨርሲቲው በኢንጅነሪንግ ዘርፍ ከጠየቀው ቁጥር በላይ የመጡ ተማሪዎችን በዚህ የትምህርት መስክ መድቧልም ነው ያሉት፤ ጥቂት ተማሪዎችም በሚቀጥለው አመት ወደ ፈለጉት የትምህርት መስክ እንደሚዛወሩ በመጥቀስ።

የትምህርት ሚኒስቴር በበኩሉ ድልድሉ የዩኒቨርሲቲዎችን የቅበላ አቅም ግምት ውስጥ በማስገባት መካሄዱን ገልጿል።

ሚኒስትር ዲኤታው ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ እንደሚሉት፥ ከዚህ ውጭ በሆነ ምክንያት በሌሎች የትምህርት መስኮች መመደብ ህጉን የተከተለ አይደለም።

ሚኒስቴሩም ተማሪዎች ያቀረቡትን ቅሬታ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር አይቶ እስከ መጭው ረቡዕ ድረስ ተገቢውን ምላሽ ይሰጣል ብለዋል።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

 

 

 

Advertisement