NEWS: በግድቡ ዙሪያ ጥናቶችን የሚያጠኑ ኩባንያዎችና የሶስቱ ሀገራት የቴክኒክ ኮሚቴዎች የሚመሩበት ረቂቅ መመሪያ ተዘጋጀ – Ethiopian Renaissance Dam

                                                      

የኢትዮጵያ፣ ሱዳንና የግብጽ የውሀ ሚኒስትሮች ያደረጉት ስብሰባ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ሁለት ጥናቶችን የሚያጠኑ ሁለት ኩባንያዎችና የሶስቱ ሀገራት የቴክኒክ ኮሚቴዎች የሚመሩበትን ረቂቅ መመሪያ በማዘጋጀት ተጠናቋል።

የሶስቱ ሀገራት የውሃ ሚኒስትሮች ዛሬ ስብሰባ ያደረጉት በሚፈለገው ደረጃ መጓዝ ያልቻሉትን ሁለት ጥናቶች ለማስቀጠል ነበር።

ሚኒስትሮቹ በውይይታቸው አማካሪ ድርጅቶቹን እና የቴክኒክ ኮሚቴውን በቀጣይ የሚመራ ረቂቅ መመሪያ አዘጋጅተዋል።

ይህም በቀጣዩ የሶስቱ ሀገራት ጉባኤ ላይ ጸድቆ ስራ ላይ ይውላል ተብሎ ይጠበቃል።

አሁን የተዘጋጀው ረቂቅ መመሪያ ጥናቱን ለማስቀጠል ይረዳል ነው የተባለው።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ አያያዝና አለቃቀቅ እንዲሁም በታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ላይ ያለው የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ እንዲጠና ነበር ሶስቱ ሀገራት ቢ አር ኤልና አርቴሊያ ከተባሉ የፈረንሳይ ኩባንያዎች ጋር ከአመት በፊት ውል የገቡት።

ሆኖም ሁለቱ ኩባንያዎች ባቀረቡት የጥናት ወሰን ላይ ከመግባባት ባለመደረሱ ጥናቱ ዘግይቷል።

 

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

 

Advertisement