የሩቅ እይታ የሚያጠቃቸው ታዳጊዎች በትምህርታቸው ላይ አሉታዊ ጫና እንደሚፈጥር ተመራማሪዎች ገለፁ

                                                    

የሩቅ የእይታ ትክተት ወይም በቅርበት ያለማየት ችግር ልጆች በትምህርታቸው ላይ ትኩረት እንዳያደርጉ አሉታዊ ጫና እንደሚፈጥር ተመራማሪዎች ገለፁ።

ይኸውም በትምህርት ሰዓት በቂ ግንዛቤ እንዳይኖራቸው እና በክፍል ውስስ በእይታ ችግር ምክንያት እንዲወድጉ ሊያደርጋቸው እንደሚችል የኦሃዮ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ያጠኑት ጥናት ያሳያል።

ያልተስተካከለ ወይም የከፋ የሩቅ እይታ ችግር ያለባቸው የቅድመ መደበኛ እና የመዋዕለ ህፃናት ተማሪዎች የመማር አቅማቸው ደካማ እና ነገሮችን የመላመድ ችሎታቸው አዝጋሚ እንደሚሆን ከዚህ በፊት የወጡ ጥናቶች ያሳያሉ።

አሁን የኦሃዩ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች በሰሩት ጥናት ደግሞ ችግሩ ከዚህም እንደሚከፋ ነው የገለፁት።

ያልተስተካከል የሩቅ እይታ ትክተት እድሜያቸው ለመደበኛ ትምህርት ያልደረሱ ህፃናት ላይ ሌሎች ጉዳቶች እንዳሉት የጠቀሱት ፕሮፌሰር ማርዥያን ቴይለር ኩልፕ ናቸው።

ከ4 እስከ 14 በመቶ ያህል የቅድመ መደበኛ ትምህርት ተማሪዎች የከፋ የሩቅ እይታ እንዳለባቸው በጥናቱ ተጠቅሷል። 

የሩቅ እይታ ትክተት ማለት ለዓይን የቀረበን ነገር በደንብ አስተካክሎ ያለማየት ችግር ነው።

ይህን ዓይነቱን ችግር ብዙ ጊዜ በምርመራ ለመለየት እና መፍትሄውን ለማስቀመጥ ያስቸግራል ብለዋል ተመራማሪዎች።

ጥናቱ የከፋ የሩቅ እይታ ችግር ያለባቸው 250 የቅድመ መደበኛ ትምህርት እና የመዋዕለ ህፃናት ተማሪዎችን እና ጤናማ የእይታ ሁኔታ ያላቸውን 250 ተማሪዎች በተመሳሳይ አካቷል።

ተመራማሪዎች በሁለት የተከፈሉትን የጥናቱ ተሳታፊ ህፃናት ያጠኑ ሲሆን፥ የሩቅ እይታ የሚያጠቃቸው ህፃናት የእይታ ትኩረታቸው፣ አቀባበላቸው እና የእይታ ችሎታቸው ደካማ መሆኑን አረጋግጠናል ነው ያሉት።

ለአብነትም የእይታ ችሎታቸው የዓይን እና የእጅ ጥምረትን በሚጠይቁ ስራዎች ላይ ደካማ ውጤት ማስመዝገባቸው ተነግሯል።

የከፋ የሩቅ እይታ የሚያጠቃቸው ህፃናት በሚመረመሩበት ጊዜ የዓይን መነፅር እንዲጠቀሙ አይመከረም፤ ምክንያቱም በዓይን መነፅር እና በልጆች የእይታ መስተካከል ላይ ስምምነት ስለማይኖር ነው ብለዋል።

ተመራማሪዎቹ አሁን ላይ የከፋ የሩቅ እይታ ወይም በቅርበት ላይ ያሉ ነገሮችን ያለማየት ችግር ያለባቸውን ህፃናት ችግር ለመቅረፍ የዓይን መነፅር አስፍላጊ ነው ወይ የሚለውን ለማጥናት የገንዘብ ድጋፍ እያፈላለጉ ነው።

የሩቅ እይታ ያለባቸው ልጆች የመማር ችሎታቸው ፈጣን እንዳይሆን እንደሚያደርግ ህብረተሰቡ ሊረዳ እንደሚገባ መክረዋል።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement