የአርጀንቲና የፈጣን አስተናጋጅ ውድድር

                                              

ዓመታዊው የአርጀንቲና ፈጣን አስተናጋጅ ውድድር በቦነስ አይረስ ከተማ ተካሂዷል።

ውድድሩን አርጀንቲና የሆቴል እና መስተንግዶ ሰራተኞች ህብረት ያዘጋጀው ሲሆን፥ ባሳለፍነው ቅዳሜ በቦነስ አይረስ ከተማ መካሄዱም ተነግሯል።

በውድድሩ ላይ 470 ወንድ እና ሴት አስተናጋጆች የተካፈሉ ሲሆን፥ በማቅረቢያ ሳህናቸው ላይ የተቀመጠውን በመጠጥ የተሞላ ብርጭቆ እና ጠርሙስ ምንም ሳይደፋ በፍጥነት ረጅም ርቀት በመሄድ ተወዳድረዋል።

በውድድሩ ላይ የተካፈሉ አስተናጋጆችም በመጠጥ የተሞሉ ብርጭቆዎችን እና ጠርሙሶችን በማቅረቢያ ሰሃናቸው ላይ በመያዝ 1 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር በፍጥነት የሚጠበቅባቸው ሲሆን፥ የውድድሩ አሸናፊም 1 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ተሸላሚ ይሆናል።

በዚህም መሰረት በሴቶች ዘርፍ የካፌ ማርቲኔዝ ቼይን አስተናጋጇ ኖዌይላ ሮጆ ውድድሩን በአንደኝነት በማጠናቀቅ 1 ሺህ የአሜሪካ ዶላሩን ወስዳ ገብታለች።

በወንዶች ከ30 ዓመት በታች ዘርፍ በተደረገው ውድድር ደግሞ በቦነስ አይረስ የጣሊያን ሆስፒታል ውስጥ ባለው ካፌ በአስተናጋጅነት የሚሰራው ካርሎስ ሴጃስ አሸናፊ ሆኗል።

የቢንጎ ላኑስ ሆቴሉ አስተናጋጅ ሊዮናርዶ ታማኖ ከ30 እስከ 45 የእድሜ ክልል የተደረገውን ውድድር ሲያሸንፍ፤ የቱሪዝሞ ሆቴል ዴ ቻዎ አስተናጋጁ ማሪያኖ ቤኒቴዝ ከ45 ዓመት በላይ የእድሜ ክልል ውድር አሸናፊ ሆኗል።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement