SPORT NEWS: የሜሲ 3 ጎሎች አርጀንቲናን ወደ ዓለም ዋንጫ አስገብተዋል

                                                        

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2018 በሩሲያ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ውድድሮች ትናንት ምሽት ቀጥለው ተካሂደዋል።

በደቡብ አሜሪካ ሀገራት መካከል በተደረገው ውድድርም እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ1970 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የመውደቅ ስጋት ተደቅኖባት የነበቸው አርጀንቲና በሜሲ አማካኝነት የዓለም ዋንጫው ላይ ለመሳተፍ የሚያስችላትን ትኬት ቆርጣለች።

ትናንት ምሽት ኢኳዶር እና አርጀንቲና ያደረጉት ጨዋታም 1ለ3 በሆነ ውጤት ነው የተጠናቀቀው።

በጨዋታው ላይ ባለሜዳዎቹ ኢኳዶሮች ጨዋታው በተጀመረ በ38ኛው ሰከንድ ላይ ባስቆጠሩት ጎል 1ለ0 መምራት የቻሉ ሲሆን፥ ይህች ጎልም የአርጀንቲናን የማለፍ ተስፋ የምታጨልም ነበረች።

ሆኖም ግን የአርጀንቲናው ሊዮኔል ሜሲ በ12ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠራት ጎል የአርጀንቲናውያንን ተስፋ ያለመለመች ሲሆን፥ ሜሲ በ20ኛው ደቂቃ እና በ62ኛው ደቂቃ ያስቆጠራቸው ጎሎች ደግሞ አርጀንቲና የዓለም ዋንጫ ላይ እንድትሳተፍ አድርጓታል።

ባስቆጠራቸው ሶስት ጎሎች ሀገሩን ለዓለም ዋንጫ ያሳለፈው ሊዮኔል ሜሲ በቀጣዩ የፈረንጆቹ 2018 የዓለም ዋንጫ ላይ ሀገሩን በመወከል ሲሳተፍም ለ4ኛ ጊዜው ይሆናል።
ትናንት ምሽት በደቡብ አሜሪካ ሀገራት መካከል በተደረጉ ሌሎች ጨዋታዎች ብራዚል ቺሊን 3ለ0 አሸንፋታላች።

ይህንን ተከትሎም ለተከታታይ ሁለት ጊዜ የኮፓ አሜሪካ ሻምፒዮኗ ቺሊ ከ2018 የዓለም ዋንጫ ውጭ መሆን ችላለች።

በሌሎች ጨዋታዎች ፓራጉዋይ ቬንዙዌላን 1ለ0፣ ኡራጉዋይ ቦሊቪያን 4ለ2 ሲያሸንፉ፤ ፔሩ እና ኮሎምቢያ 1ለ1 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይተዋል።

የትናንት ምሽቱን የጨዋታ ውጤቶች ተከትሎም ብራዚል፣ ኡራጉዋይ፣ አርጀንቲና እና ኮሎምቢያ ከደቡብ አሜሪካ ሀገራት የዓለም ዋንጫ ላይ እንደሚሳተፉ አረጋግጠዋል።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement