SPORT NEWS: የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሞሮኮ አቻው ተረታ

                                                           

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ትናንት ምሽት ራባት ላይ ከሞሮኮ የቻን ብሔራዊ ቡድን ጋር ባደረገው የወዳጅነት ጨዋታ 4ለ0 በሆነ ውጤት ተሸንፏል፡፡

የሞሮኮ እግርኳስ ፌዴሬሽን ባቀረበው የወዳጅነት ጨዋታ ግብዣ መሰረት ማክሰኞ ይደረጋል የተባለው ጨዋታ ባልታወቀ ምክንያት ትናንት ተካሂዷል፡፡ 

ወደ ጋቦሮኒ አቅንቶ በቦትስዋና የተሸነፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሰኔ ወር ጀምሮ በሁሉም ውድድሮች በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ እየተመራ ካደረጋቸው 8 ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው 1 ጨዋታ ሲሆን፥ ይህም ጅቡቲን ብቻ ነው፡፡

ሞሮኮ እና ዋልያዎቹ ባደረጉት ጨዋታ የመጀመሪያውን አጋማሽ ሞሮኮ 3ለ0 እየመራች ለእረፍት ወጥተዋል።

ከእረፍት መልስ ዋልያዎቹ ተጨማሪ አንድ ግብ በማስተናገድ 4ለ0 ተሸንፈዋል።

የፊት መስመር ተሰላፊው ጌታነህ ከበደ በሁለት ቢጫ ከሜዳ በተሰናበተበት በዚህ ጨዋታ ላይ አሰልጣኝ አሸናፊ ተጫዋቾቹን ከተፈጥሯዊ ቦታቸው በመቀየር ለማጫወት ሞክረዋል፡፡ 

ለዚህ ማሳያው የመስመር አጥቂ የሆነው አዲስ ግደይ ባዬ ገዛኸኝን ቀይሮ ወደ ሜዳ ከገባ በኃላ በቀኝ መስመር ተከላካይ ቦታ ላይ ተጫውቷል፡፡ 

በተጨማሪም ቡድኑ ወደ ራባት ያቀናው 15 ተጫዋቾችን ብቻ ይዞ ሲሆን፥ ከእነዚህ ውስጥ ሶስቱ ግብ ጠባቂዎች ነበሩ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በተደጋጋሚ በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ሽንፈት ማስተናገዱን ቀጥሏል፡፡ 

ቡድኑ በሐምሌ ወር ጅቡቲን በቻን ማጣሪያ 5ለ1 ያሸነፈበት ውጤት ብቻ ድል ሆኖ ሲመዘገብ፥ በቀሪዎቹ 7 ጨዋታዎች 4 ሲሸነፍ 3 አቻ ተለያይቷል፡፡

የብሔራዊ ቡድኑ ከሰኔ ወር ጀምሮ ያስመዘገባቸው ውጤቶች እነዚህን ይመስላሉ

ኢትዮጵያ 0-0 ዩጋንዳ (የወዳጅነት)

ጋና 5-0 ኢትዮጵያ (የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ)

ጅቡቲ 1-5 ኢትዮጵያ (የቻን ማጣሪያ)

ዛምቢያ 0-0 ኢትዮጵያ (የወዳጅነት)

ኢትዮጵያ 1-1 ሱዳን (የቻን ማጣሪያ)

ሱዳን 1-0 ኢትዮጵያ (የቻን ማጣሪያ)

ቦትስዋና 2-0 ኢትዮጵያ (ወዳጅነት)

ሞሮኮ 4-0 ኢትዮጵያ (የወዳጅነት)

 

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

 

Advertisement