NEWS: በድንበር የሚካሄድ ኮንትሮባንድ የአገር ፈተና ሆኗል

                                                    

  • ሕገወጥ የመድኃኒት ዝውውር የጤና ዋስትና ሥጋት መሆኑ ተገለጸ

ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገሮች ጋር በምትዋሰንባቸው የድንበር ንግድ ቀጣናዎች የሚካሄደው ሕገወጥ ንግድ፣ አገሪቱን ለውጭ ምንዛሪ ኪሳራና ለማኅበራዊ ደኅንነት ችግር እየዳረገ መሆኑ ተመለከተ፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የተቋቋመውና በርካታ የዘርፍ መሥሪያ ቤቶችን ያካተተው የፀረ ኮንትሮባንድና ሕገወጥ ንግድ መከላከል ግብረ ኃይል፣ ሰሞኑን በአዳማ ከተማ በዚህ ጉዳይ ላይ መክሯል፡፡

ይኼንን ውይይት የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትሩ አቶ ዓለማየሁ ተገኑና የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሞገስ ባልቻ መርተዋል፡፡

ዘጠኙም ክልሎችና ሁለቱ የከተማ መስተዳድሮች የ2009 ዓ.ም. ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን፣ በአጠቃላይ በኮንትሮባንድና በሕገወጥ ንግድ ላይ ለሁለት ቀናት ውይይት ተደርጓል፡፡

አቶ ሞገስ እንደገለጹት፣ በኮንትሮባንድ በርካታ ዕቃዎች እየገቡና እየወጡ ነው፡፡ ይኼም አገሪቱን በከፍተኛ ደረጃ የውጭ ምንዛሪ እያሳጣና በማኅበራዊ ደኅንነት ላይም ችግር እየፈጠረ ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ኤክስፖርት አድርጋ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ልታገኝ ከምትችልባቸው የግብርና ምርቶች መካከል የቁም እንስሳት፣ ቡናና የተለያዩ የቅባት እህሎች፣ ወርቅ፣ ኦፖልና ኤመራልድን ጨምሮ የተለያዩ ውድ ማዕድናት በሕገወጥ መንገድ ከአገር እየወጡ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

ከውጭ ደግሞ ታክስ ሊከፈልባቸው የሚገቡ በርካታ የኢንዱስትሪ ምርቶች፣ ደረጃቸውን ያልጠበቁና የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው መድኃኒቶችና ምግቦች ወደ አገር እንደሚገቡ ተገልጿል፡፡

በውይይቱ ወቅት እንደተነሳው የገቢና የወጪ ኮንትሮባንድ ንግድ አገሪቱ በርካታ የውጭ ምንዛሪ እንድታጣ ከማድረጉም በላይ፣ ሕገወጥ የመድኃኒት ዝውውር የማኅበረሰቡን የጤና ዋስትና አደጋ ውስጥ ከቶታል፡፡

የኢትዮጵያ የምግብ መድኃኒትና ጤና ክብካቤ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወ/ሪት ሄራን ገረባ በውይይቱ ወቅት እንደገለጹት፣ የሕገወጥ መድኃኒት ዝውውርና የምግብና የመድኃኒት ጥራት መጓደል የኅብረተሰብን ጤና አደጋ ውስጥ ከቶታል፡፡ በችግሩ ምክንያት በርካታ ሰዎች አልጋ እየያዙ ነው፡፡

‹‹የመድኃኒትና የምግብ ጥራት መጓደል ከአሸባሪነትም በላይ ነው፤›› ሲሉ የችግሩን ክብደት ገልጸውታል፡፡

የፖለቲካ ቁርጠኝነት መሳሳት፣ የፍትሕ አካላት በጥፋተኞች ላይ ተገቢውን ቅጣት አለመጣል፣ የፀጥታ አካላት ቁርጠኛ አለመሆን፣ የተወሰኑትም ለድርጊቱ ተባባሪ መሆን ተጠቃሽ ችግሮች ሆነው ቀርበዋል፡፡

‹‹ያለ ፖለቲካ ትግል ኮንትሮባንድንና ሕገወጥ ንግድን ማቆም አስቸጋሪ ነው ጉዳዩ ያለ ፖለቲካ ቁርጠኝነት የሚስተካከል ባለመሆኑ ቁርጠኛ መሆን ያስፈልጋል፤›› ሲሉ አቶ ሞገስ የችግሩን ስፋት ገልጸዋል፡፡

የፍትሕ ተቋማት ደግሞ በኮንትሮባንድና በሕገወጥ ንግድ ተሰማርተው በተገኙ አካላት ላይ ለጉዳዩ በቂ ክብደት እየሰጡ አለመሆኑም ተገልጿል፡፡ ‹‹የፍትሕ ተቋማት የኮንትሮባንድና የሕገወጥ ንግድ በአገሪቱ ሰላም፣ ልማት እንዲሁም በሰው ልጆች ጤና ላይ የሚያሳድሩትን ተፅዕኖ ያለማስተዋል ችግር ታይቷል፡፡ ለተጠያቂዎች የሚሰጠው ዋስትናና ቅጣት ለዛቻ ከሚሰጠው ቅጣት ጋር እኩል ነው፤›› ሲሉ አንድ የግብረ ኃይሉ አባል ተናግረዋል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር አሰፋ በዩ በወቅቱ እንደገለጹት በፌዴራል ፖሊስ፣ በክልል ፖሊስና በጉምሩክ መዋቅሮች እጃቸውን ያስገቡ አካላት አሉ፡፡

‹‹በፌዴራል ፖሊስ በኩል ከ80 በላይ አመራሮችና አባላት ተይዘው ዕርምጃ ተወስዶባቸዋል፡፡ በክልሎችም ተመሳሳይ ዕርምጃ ተወስዷል፤›› ሲሉ ኮሚሽነር አሰፋ ተናግረዋል፡፡

የዛሬ ዓመት መስከረም 30 ቀን 2009 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በተገኙበት የተካሄደው የብሔራዊ የኤክስፖርት አስተባባሪ ኮሚቴ ስብሰባ የኮንትሮባንድ ንግድ አሪቱን ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈለ በመሆኑ፣ ሕገወጥ ንግዱን ለመከላከል የተቋቋመው ግብረ ኃይልና ኮማንድ ፖስት ይኼን ችግር እንዲፈቱ ኃላፊነት ሰጥቶ ነበር፡፡

በተለይ ወርቅ የት እንደሚሄድ፣ እንዴት እንደሚሄድ፣ በየት በኩል እንደሚሄድ፣ ማን እንደሚረከብ እንዲታወቅና ዕርምጃ እንዲወሰድ ኮሚቴው መመርያ አውጥቶ ነበር፡፡

በከፍተኛ መጠን ወደ ውጭ የሚወጣውን የወርቅ ኔትወርክ በመበጣጠስ የኮንትሮባንድ ንግዱን የመቆጣጠር ጉዳይ እንዲጠናከር፣ በዚህ ረገድ ከፀረ ኮንትሮባንድ ግብረ ኃይል ጋር የሚደረገው ቅንጅት በዕቅድ ላይ ተመሥርቶ እንዲካሄድ፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራው የኤክስፖርት አስተባባሪ ኮሚቴ መመርያ ሰጥቶ ነበር፡፡

ነገር ግን ይኼ መመርያ ከተሰጠ ከዓመት በኋላ በተካሄደው የግብረ ኃይሉ ስብሰባ አሁንም የወርቅ ኮንትሮባንድ መቀጠሉ ተመልክቷል፡፡

የማዕድን፣ ነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ቴዎድሮስ ገብረ እግዚአብሔር በወቅቱ እንደገለጹት፣ ወርቅ የመግዛት ሥልጣን የተሰጠው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከዓለም ገበያ ዋጋ አምስት በመቶ ጭማሪ አድርጎ ይገዛል፡፡

‹‹ነገር ግን ኮንትሮባንዲስቶች ከዚህ በላይ እየከፈሉ ማዕድኑን ኬንያ፣ ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ዱባይ፣ ቻይና፣ ህንድ ወስደው ይሸጡታል፤›› ሲሉ የችግሩን ስፋት ገልጸዋል፡፡

‹‹በተለይ ወርቅ አነስተኛ ሆኖ ትልቅ ገንዘብ የሚያወጣ በመሆኑ ችግሩ ጎልቷል፤›› ሲሉ አቶ ቴዎድሮስ አስረድተዋል፡፡

የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትሩ አቶ ዓለማየሁ ተገኑ እንደገለጹት፣ የኮንትሮባንድ ንግድና ሕገወጥ ንግድ የማይቀለበስ ችግር አይደለም፡፡ ይኼ ችግር ካልተቀለበሰ ግን ከፍተኛ አደጋ ስላለው በቅንጅት ሊሠራ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

 

ምንጭ:- ሪፖርተር

   

Advertisement