በኢትዮጵያ በየዓመቱ በጡት ካንሰር ከሚጠቁት 13 ሺህ ሰዎች ወስጥ 53 በመቶዎቹ ለሞት ይዳረጋሉ ተባለ

                                                        

በኢትዮጵያ በየዓመቱ ለጡት ካንሰር ከሚጋለጡ 13 ሺህ ሰዎች ውስጥ 7 ሺህ ያህሉ ለሞት እንደሚዳረጉ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ህብረተሰቡ ለጡት ካንሰር ያለው የግንዛቤ ማነስና ህክምናውን የሚሰጡ የጤና ተቋማት በቂ አለመሆን በሽታውን በቀላሉ መከላከል እንዳይቻል ማድረጉንም ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

የጡት ካንሰር በቅድሚያ በጡት ላይ በመከሰት ወደ ሌሎች የሰውነት ክፍሎች በመዛመት ለሞት የሚያጋልጥ በሽታ ሲሆን፥ በሽታው በዋናነት ሴቶችን የሚያጠቃ ይሁን እንጅ አልፎ አልፎ ወንዶችንም ያጠቃል። 

በኢትዮጵያ በየዓመቱ 13 ሺህ ሰዎች ለጡት ካንሰር የሚጋለጡ ሲሆን፥ ከነዚህ ውስጥ 7 ሺህ ያህሉ እንደሚሞቱ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የጥቅምት ወር በዓለም አቀፍ ደረጃ የጡት ካንሰርን በተመለከተ ግንዛቤ ማስጨበጫ ወር ሆኖ ይቆያል።

ይህን አስመልክቶ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከቀዳማዊት እመቤት ፅህፈት ቤት ጋር ትናንት በሰጡት መግለጫ ማህበረሰቡ ስለ በሸታው ያለው ግንዛቤ በቂ ባለመሆኑ ተጋላጭነቱን መቀነስ አለመቻሉ ተገልጿል።

የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ፕሮፌሰር ይፍሩ ብርሃነ፥ ኢትዮጵያ በዚሁ በሽታ ከሚጠቁ አዳጊ አገራት አንዷ መሆኗን ጠቅሰው የህብረተሰቡ የግንዛቤ ማነስ ዋነኛው ችግር መሆኑን ገልፀዋል።

የጡት ካንሰር መንስኤዎች

  • የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ
  • ጡት አለማጥባት፣ ሲጋራ ማጨስ
  • አልኮል መጠጣት
  • ከሆርሞን ጋር የተያያዙ መድሀኒቶችን መውሰድ
  • ቶሎ አለመውለድ እና ሌሎቹ ምክንያቶች ለጡት ካንሰር መንስኤዎች ናቸው።

የጡት ካንሰር ተጋላጭነትን ለመቀነስ

  • በየቀኑ የአካል እንቅስቃሴ በማድረግ
  • ከ1 ዓመት እስከ 2 ዓመት ጡት ማጥባት
  • ከ20 እስከ 30 መካከል ባለው እድሜ ልጅ በመውለድ ተጋላጭነትን መቀነስ እንደሚቻል ፕሮፌሰር ይፍሩ ተናግረዋል።

የጡት ካንሰር ምርመራውም ሆነ ህክምናው በጣም ከፍተኛ ወጪ ስለሚጠይቅና ህይዎትን ሊያሳጣ ስለሚችል ሕብረተሰቡ ቅድመ ምርመራ በማድረግ መከላከል እንዳለበት አሳስበዋል።

ሚኒስቴሩም በብሄራዊ ካንሰር መቆጣጠሪያ ስትራቴጂ እየተመራ እንደማንኛውም በሽታ መከላከሉ ላይ ትኩረት ለማድረግ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ እየሰራ ነው ብለዋል።

በቅድመ ምርመራ ከተቻለ ቀድሞ ለመከላከል ካልሆነም በሽታውን ቀድሞ በማወቅ ወደ ህክምና እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

ሚኒስትሩ አሁን ላይ 12 የመንግስት ሆስፒታሎች ህክምናውን እየሰጡ መሆኑን ጠቅሰው የህክምና ማዕከላት እጥረትን ለመቀነስ ተጨማሪ ስድስት የህክምና ማዕከላት እየተገነቡ መሆኑን ገልፀዋል።

የግል ህክምና ተቋማት ህክምናውን እንዲሰጡ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ሚንስትሩ ሐኪሞችን በተጓዳኝነት ስለ በሽታው በማሰልጠን እንዲመረምሩና ህክምና እንዲሰጡ እየተደረገ ነውም ብለዋል።

የዘንድሮው የግንዛቤ ማስጨበጫ ወር በኢትዮጵያ ”የጡት ካንሰር በሽታን መከላከል የሁላችንም ሀላፊነት ነው፤ጡትዎን በመዳሰስና ቅድመ ምርመራ በማድረግ ህይዎትዎን ይታደጉ” በሚል መሪ ሀሳብ ለ11ኛ ጊዜ ይከበራል።

 

ምንጭ:- ጤናችን

 

Advertisement