የብር የውጭ ምንዛሬ ዋጋ ከነገ ጀምሮ በ15 በመቶ ይዳከማል – ብሔራዊ ባንክ

 

                                                                  

በካሳዬ ወልዴ

የወጪ ንግድን ለማሳደግ ሲባል ከነገ ጀምሮ የብር የውጭ ምንዛሬ ዋጋ በ15 በመቶ እንዲቀንስ እንደሚደረግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገለፀ።

ዝቅተኛ የባንኮች የቁጠባ ሂሳብ የወለድ ተመንም ከ5 በመቶ ወደ 7 በመቶ ከፍ እንዲል እንደሚደረግ ነው ባንኩ የገለፀው።

በዚህ ጉዳይ ላይ የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ እና ዋና ኢኮኖሚስት ዶክተር ዮሀንስ አያሌው መግለጫ ሰጥተዋል።

በኢትዮጵያ የወጪ ንግድ እንቅስቃሴ ከ1996 እስከ 2004 በነበሩት 8 ዓመታት በፍጥነት ያድግ እንደነበር በመግለጫው ጠቅሰዋል።

ዓመታዊ አማካይ የእድገት ምጣኔውም 24 ነጥብ 1 በመቶ ነበር ብለዋል።

ነገርግን ከ2005 እስከ 2009 ባሉት 5 ዓመታት በዓለም ገበያ የሸቀጦች ዋጋ በከፍተኛ እና በተከታታይ ሁኔታ በመቀነሱ እና የአሜሪካ ዶላር ከሌሎች የኢትዮጵያ የንግድ ሸሪክ ሀገራት ገንዘቦች ጋር ያለው ምንዛሬ በከፍተኛ መጠን በመጠንከሩ ምክንያት የወጪ ንግድ እድገቱ ተቀዛቅዟል።

በተለይም በቡና፣ የቅባት እህል፣ ጥራጥሬ፣ ቆዳ እና የቆዳ ውጤቶች እንዲሁም ወርቅ በዚህ ምክንያት ከፍተኛ የዋጋ መቀነስ ያጋጠማቸው ምርቶች መሆናቸውን ነው የጠቀሱት።

መንግስት ባለፉት 5 ዓመታት በዓለም የሸቀጦች ዋጋ መቀነስ ምክንያት የተቀዛቀዘውን የሀገሪቱን የወጪ ንግድ ገቢ ለማካካስ ርብርብ በማድረጉ የገቢ ውድቀትን ለማስቀረት መቻሉን ባንኩ አንስቷል።

ሆኖም የ2008 እና የ2009 በጀት ዓመት የሸቀጦች የወጪ ንግድ አፈፃፀም መቀዛቀዝ ታይቶበታል።

በመሆኑም መንግስት በ2010 በጀት ዓመት የተቀመጡ ግቦችን ሳይሸራረፉ ለማሳካት ከግብርና፣ ከኢንዱስትሪ፣ ከማዕድን እና ከአገልግሎት ዘርፍ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ በማሳደግ እየሰፋ የመጣውን የንግድ ሚዛን ለማጥበብ ዝግጅት አድርጎ በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑን ዶክተር ዮሐንስ ተናግረዋል።

በማክሮ ኢኮኖሚ በኩል የወጪ ንግድ ምርቶችን ተወዳዳሪነት ለማጠናከር እና ሀገራዊ ቁጠባን ለማሳደግ የሚረዱ ፖሊሲዎችን መቅረፅ በማስፈለጉ የውጭ ምንዛሬ እና የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያዎች መደረጉን ገልፀዋል።

በዚህም መሰረት ከነገ ጥቅምት 1 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ የብር የውጭ የምንዛሬ ዋጋ በ15 በመቶ እንዲቀንስ ተደርጓል ነው ያሉት።

በማስተካከያው መሰረትም ለምሳሌ ዛሬ 1 የአሜሪካ ዶላር የመግዣ ዋጋው 23 ነጥብ 4177 ብር ከሆነ፥ ነገ በምንዛሬ ተመኑ ላይ የ15 በመቶ ጭማሪ ተደርጎ 26 ነጥብ 9303 ብር የመግዣ ዋጋው ይሆናል ማለት ነው።

ዝቅተኛ የባንኮች የቁጠባ ሂሳብ የወለድ ተመንም ከነገ ጀምሮ ከ5 በመቶ ወደ 7 በመቶ ከፍ እንዲል ይደረጋል ብሏል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ።

ከሰባት ዓመት በፊት በብር የውጭ ምንዛሬ ተመን ላይ የ17 በመቶ ማስተካከያ ያደረገችው አገሪቱ፥ መሰል እርምጃ እንድትወስድ በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ስትጎተጎት ቆይታለች።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

 

 

Advertisement