NEWS: በምግብ ውስጥ የሚገኝን የካሎሪ መጠን ማወቅ የሚያስችል መሳሪያ ተዋወቀ

                                                      

እንደ ስኳር ባሉ በሽታዎች የተጠቁ ሰዎች አመጋገባቸውን መቆጣጠርና የሚመገቡትን ምግብ መጠንም ማስተካከል ይገባቸዋል።

በከፍተኛ ውፍረት የተቸገሩ ሰዎችም አመጋገባቸውንና የሚገቡትን የምግብ አይነት መመጠንና ማስተካከል እንደሚገባቸው የህክምና ባለሙያዎች ይመክራሉ።

ከዚህ ባለፈም በሚመገቡት ምግብ ውስጥ ያሉ ንጥረ ነገሮችን መጠንና አይነት ማወቁም እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ነው የሚናገሩት።

የቴክኖሎጅ ኩባንያዎችም በመሰል ችግሮች ለሚጠቁ ሰዎች አመጋገባቸውን መቆጣጠርና ማስተካከል የሚችሉባቸውን መንገዶች ለማመቻቸት የተለያዩ ፈጠራዎችን እያስተዋወቁ ነው።

ፓናሶኒክም በሚመገቡት ምግብ ውስጥ ያለውን የካሎሪና ሌሎች ንጥረ ምግቦችን መጠን ማወቅ የሚያስችል መሳሪያ መስራቱን አስታውቋል።

መሳሪያው አንድ ሰው ሊመገብ ባዘጋጀው ምግብ ውስጥ ያለውን የካሎሪና ሌሎች ንጥረ ምግቦች መጠን ለማወቅ የሚረዳ ሲሆን፥ አመጋገባቸውን ለማስተካከል ለሚሞክሩ ሰዎችም ትልቅ የምስራች ነው ተብሏል።

ካሎሪየኮ የተባለው መሳሪያ በ2017ቱ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ግኝቶች ማሳያ አውደ ርዕይ ላይ የቀረበ ሲሆን፥ ትክክለኛ መረጃ መስጠት ያስችላል ነው የተባለው።

አገልግሎቱን ማግኘት የሚፈልጉ ተጠቃሚዎች የሚመገቡትን ምግብ የያዘውን ሳህን በአነስተኛ የሳጥን ቅርጽ በተሰራው መሳሪያ ውስጥ ማስቀመጥ ይጠበቅባቸዋል።

መሳሪያውም ሰሃኑ ላይ በሚያሳርፈው ብርሃን አማካኝነት ምግቡ ውስጥ ያለውን የካሎሪና የሌሎች ንጥረ ምግቦች መጠንን ይለያል ተብሏል።

መሳሪያው ከ10 እስከ 20 ሰከንዶች ባለው ጊዜ ውስጥም ውጤቱን ለተጠቃሚዎች ያሳውቃል።

የንጥረ ምግቡን መጠን ከለየ በኋላም በተገጠመለት አነስተኛ ስክሪን ላይ የሚያሳይ ይሆናል።

አዲሱ መሳሪያ ታዲያ ከሾርባ እና በበዛ መልኩ ተጠብሰውቸ በሚዘጋጁ ምግቦች ውጭ በሌሎች ምግቦች ውስጥ የሚገኝን የካሎሪና ተያየያዥ ንጥረ ምግቦች መጠን ለማወቅ ያስችላል።

መሳሪያው ተገልጋዮች በቀላሉ ይጠቀሙበት ዘንድም ከስማርት ስልኮች ጋር በመተግበሪያ አማካኝነት መገናኘት ይችላል።

ይህ መሆኑ ደግሞ ተገልጋዮች በቀላሉና በፈለጉት ቦታ ያገኙት ዘንድ አጋጣሚዎችን ይፈጥርላቸዋል።

እንደ ፓናሶኒክ ገለጻ መሳሪያው ለስኳር በሽተኞችና አመጋገባቸውን እንዲያስተካክሉ ለተነገራቸው ሰዎች ታስቦ የተሰራ ሲሆን፥ አሁን ላይ ለዕይታ ከመቅረቡ ውጭ ለገባያ ስለሚወጣበት ቀንና ስለዋጋው አልተገለጸም።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement