NEWS: የአዋሽ ወንዝ ባስከተለው የጎርፍ አደጋ ከተፈናቀሉት ውስጥ ከ14 ሺህ በላይ ሰዎች ወደ ቀያቸው ተመልሰዋል

                                                     

የአዋሽ ወንዝ መሙላት ባስከተለው የጎርፍ አደጋ ከተፈናቀሉት ውስጥ ከ14 ሺህ 600 በላይ ሰዎች ወደ ቀያቸው መመለሳቸውን የኦሮሚያ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ገለፀ።

በጎርፍ አደጋው ምክንያት ከቀያቸው የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር 20 ሺህ እንደነበረም ኮሚሽኑ ገልጿል።

በወንዙ መሙላት ምክንያት ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች፥ የጎርፍ አደጋው በመኖሪያ ቤታቸው እና በማሳቸው ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ነው የሚናገሩት።

በአሁኑ ጊዜም መንግስት የተለያየ ድጋፍ እያደረገልን ነው ያሉት ነዋሪዎቹ፥ ይህ ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

የምስራቅ ሸዋ ዞን የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ጄይላን አህመድ፥ በዞኑ አዋሽ ወንዝን ከሚያዋስኑ ስድስት ወረዳዎች ውስጥ አምስቱ የጎርፍ አደጋ ጉዳት እንደረሰባቸው ገልጸዋል።

32 ሺህ 250 የህብረተሰብ ክፍሎች የጎፍር አደጋው ሰለባ መሆናቸውን የገለጹት ሃላፊው፥ አደጋው በንብረት እና መኖሪያ ቤቶች ላይ ጉዳት ቢያደርስም የሰው ህይወት አለማለፉን ተናግረዋል።

በአምስቱ ወረዳዎች 108 ስምንት ቤቶች ፈርሰዋል ያሉት ሃላፊው፥ በመተሃራ ከተማ ላይ ደግሞ 185 ቤቶች በጎርፍ አደጋው ፈርሰዋል፤ ሌሎች በርካታ ቤቶች ላይ ደግሞ ጉዳት ደርሷል ብለዋል።

ከ6 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ ላይ የጎርፍ ውሃው በመተኛት ሰብል ጉዳት ማድረሱንም አስታውቀዋል። 

በአጋው ወቅት በርካታ የቤት እንስሳትን ከአደጋው ለመታደግ የተቻለ ቢሆንም፥ 210 የተለያዩ የቤት እንስሳቶች በጎርፍ አደጋው ተወስደዋል።

በአሁኑ ጊዜም ከቆቃ በላይ ያሉ አካባቢዎች ላይ የውሃ መጠኑ መቀነስ አሳይታል ያሉ ሲሆን፥ ከቆቃ በታች አዳማ፣ ቦሰት እና ፈንታሌ ወረዳዎች አሁንም የውሃ መጠኑ አልቀነሰም ነው ያሉት አቶ ጄይላን።

ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ እና ማሳቸው ለወደመባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ከፌደራል መንግስት እና ከክልሉ መንግስት የተገኝ እህል፣ ዘይት እና አልሚ ምግብ እየተከፋፈለ መሆኑንም ገልጸዋል።

የኦሮሚያ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የኮሙዩኒኬሽን ጉዳይ ሃላፊ አቶ ግርማ ዋከኔ በበኩላቸው፥ በ65 ቀበሌዎች ላይ የተከሰተው የጎርፍ አደጋ በርካታ ጉዳት አድርሷል ብለዋል።

በጎርፉ ምክንያትም ከ20 ሺህ በላይ ሰዎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን ገልጸው፥ ከእነዚህ ውስጥ የጎርፍ ውሃው መቀነስ በታየባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ከ14 ሺህ 600 በላይ ሰዎች ወደ ቤታቸው መመለሳቸውን ተናግረዋል።

በአደጋው ማሳቸው ለወደመባቸው አርሶ አደሮች በ40 ሚሊየን ብር የዘር ግዢ በመፈፀም ድጋፍ እንደሚደረግላቸዉ ኮሚሽኑ አስታውቀዋል።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement