በሎተሪ ትኬት ግዥ ከሚስቱ ቁጣ የገጠመው ግለሰብ የ1 ሚሊየን ዶላር አሸናፊ ሆነ

                                                      

በርካታ የሎተሪ ትኬቶችን በመግዛቱ የሚስቱን ቁጣ ያስተናገደው ግለሰብ የ1 ሚሊየን ዶላር አሸናፊ ሆኗል።

ግለሰቡ የካሊፎርንያ ነዋሪ ሲሆን ሄርመንጊልዶ ቤልትራን-ሜዛ ይባላል።

ሰውየው ሁል ጊዜ የሚፋቁ የሎቶ ሎተሪ ትኬቶችን እየገዛ እድሉን ይሞክራል።

የሚገዛቸውን ሎተሪዎች ፍቆ ሳያሸንፍ ሲቀር በገላ መታጠቢያ ክፍል ውስጥ ደብቆ ያስቀምጣል።

ከዕለታት በአንዱ ቀን ሚስቱ የሎተሪ ትኬቶችን ታገኝ እና በባሏ ድርጊት ተበሳጭታ ከድርጊቱ እንዲቆጠብ ታስጠነቅቀዋለች።

አንድ ቀን ታዲያ ቤልትራን-ሜዛ ሁለት “የካሊፎርኒያ ብላክ ፕሪሚየም” የሚፋቁ ሎተሪዎች እያንዳንዳቸውን በ10 የአሜሪካ ዶላር ይገዛል።

የመጀሪያውን ሲፍቀው እድል ሳይኖረው ይቀራል፤ ሁለተኛው የብላክ ፕሪሚየም የሎቶ ትኬት ግን እድሉን አላዞረበትም።

ሲፍቀውም በትኬቱ የ1 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር አሸናፊ መሆኑን ያረጋግጣል።

በዚህም ባል ሎተሪ በተደጋጋሚ በመግዛቱ የተቆጣችውን ባለቤቱን በመጨረሻ ባገኘው ሽልማት አፅናንቷል ነው የተባለው።

“ አንቺ ሁል ጊዜ እንዳማላሸንፍ ትነግሪኝ ነበር፤ ሆኖም ይኸው በመጨረሻ አሸነፍኩ” ብሏል።

ብዙ ትኬቶችን በመግዛቱ ከሚስቱ ጋር ቢጋጭም አሁን በደረሰው የሎተሪ እድል በተገኘው ገንዘብ ባል እና ሚስቱ ደስተኛ መሆናቸው ተነግሯል።

1 ሚሊየን ዶላሩንም ለጡረታ እንደሚያስቀምጡት ተናግረዋል።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement