NEWS: ኢትዮጵያና አሜሪካ ታሪካዊ ግንኙነታቸውን በተለያዩ ዘርፎች እንደሚያጠናክሩ ገለፁ

                                                                                        

ኢትዮጵያና አሜሪካ ታሪካዊ ግንኙነታቸውን በተለያዩ ዘርፎች አጠናክረው ለማስቀጠል እንደሚሰሩ ገለጹ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ አዲስ ከተሾሙት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክል ራይነር ጋር ተወያይተዋል። 

አምባሳደር ማይክል ራይነር የሹመት ደብዳቤያቸውን ለዶክተር ወርቅነህ አቅርበዋል።

ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ላላት ግንኙነት ታላቅ ግምት እንደምትሰጥ ዶክተር ወርቅነህ ለአምባሳደር ራይነር ገልጸውላቸዋል።

ሁለቱ ሀገራት ዘመናትን የተሻገረ ግንኙነት እንዳላቸውና ግንኙነቱም በየጊዜው በተለያዩ ዘርፎች እያደገ መሆኑንም ተናግረዋል።

በንግድና ኢንቨስትመንት ረገድ በቀጣይ ሰፊ ስራዎችን በጋራ መስራት እንዳለባቸው ነው የጠቆሙት።

የአሜሪካ ባለሃብቶች ኢትዮጵያ ባላት ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጮች ቢሳተፉ ውጤታማ እንደሚሆኑም ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን በሚደረገው ጥረት አሜሪካ ሚናዋን እንድታጠናከር ነው ዶክተር ወርቅነህ የጠየቁት።

አምባሳደር ራይነር በበኩላቸው በአዲሱ የአሜሪካ አስተዳደር በኩል ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ትብብር አጠናክሮ ለማስቀጠል ዝግጁነት መኖሩን አብራርተዋል።

አሜሪካ በኢንቨስትመንት እና በቴክኖሎጂ ሽግግር ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ወዳጅነት የማሳደግ ጽኑ ፍላጎት እንዳላት ነው አምባሳደሩ ያነሱት።

ኢትዮጵያ በቀጠናው ሰላምን ለማስፈን የምታደርገውን ጥረት ያደነቁት አምበሳደር ራይነር፥ አሜሪካ የዚህ ጥረት አጋርነቷን አጠናክራ እንደምትጥቀጥል ገልጸዋል።

በተመሳሳይ ዜና አዲስ የተሾሙት በኢትዮጰያ የጆርዳን አምባሳደር ዶክተር ዋሲፍ አያድ የሹመት ደብዳቤያቸውን ለዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ አቅርበዋል።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement