NEWS: አትሌት አልማዝ አያና በዓመቱ ምርጥ 20 የዓለም አትሌቶች ዝርዝር ተካተተች

                                                                      

 

አትሌት አልማዝ አያና የ2017 በዓለም ምርጥ 20 አትሌቶች ዝርዝር ውስጥ ተካተተች።

ዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር በሴቶችና ወንዶች የዓመቱን ምርጥ 20 ዕጩ አትሌቶች ዛሬ ይፋ አድርጓል።

በለንደን በተካሄደው 16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ10 ሺህ ሜትር ሴቶች ለኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳሊያ ያስገኘችው አትሌት አልማዝ አያናም ከሴቶች ምድብ በአንደኝነት ተመርጣለች።

ከአልማዝ በመቀጠል የከፍታ ዝላይ ተወዳዳሪ የሆነችው ማሪያ ላስቲስኬን ከሩሲያ፣ ኬንያዊቷ የረጅም ርቀት ተወዳዳሪ ሄለን ኦቢሪ እንዲሁም አውስትራሊያዊቷ የመሰናክል ተወዳዳሪ ሳሊ ፒርሰን በምርጫው ተካተዋል።

ሳንድራ ፔርኮቪች፣ደቡብ አፍሪካዊቷ ካስተር ሴሜኒያ እና ብሪትኒ ሪስም በዕጩነት ተካተዋል።

በወንዶች ደቡብ አፍሪካዊው የአጭር ርቀት ተወዳዳሪ ዋይድ ቫን ኒከርክ፣ ፖላንዳዊው የመዶሻ ውርወራ ተወዳዳሪ ፓወል ፋጄክ፣ አሜሪካዊው የምርኩዝ ዝላይ ተወዳዳሪ ሳም ሄንድሪክስ፣ ሞ ፋራህ እና ኬንያዊው ሯጭ ኤሊያህ ማናንጎይም በዝርዝሩ መካተት ችለዋል።

በዕጩነት ከቀረቡ 20 አትሌቶች መካከል የተሻለ ደምጽ የሚያገኙት የፊታችን ታህሳስ ወር በወንድና በሴት ምርጥ የሚለውን ስያሜ ያገኛሉ።

ባለፈው አመት በሴቶች አልማዝ አያና በወንዶች ደግሞ ጃማይካዊው ዩዜን ቦልት የዓመቱ ምርጥ አትሌቶች በመባል መመረጣቸው ይታወሳል።

ምንጭ:- FBC  (ኤፍ ቢ ሲ)

 

Advertisement