ሄፖታይተስ ቢ

                                                 

ሄፖታይተስ ምንድን ነው?
ሄፖታይተስ ማለት ከጉበት መቆጣት ጋር የተያያዘ የጉበት ጉዳት ማለት ሲሆን ፤ይህ የጉበት መቆጣት በሁለት ይከፈላል፡፡ የመጀመሪያው ድንገተኛ ሄፖታይተስ (Acute) ይባላል፡፡ሁለተኛው ደግሞ ስር የሰደደ የቆየ የጉበት መቆጣት (Chronic) ሲባል የህመሙ ምልክቶች ስድስት ወርና ከእዚያ በላይ ሲቆይ የሚከሰቱ ናቸው፡፡ የመጀመሪያው ድንገተኛው ሄፖታይተስ በቀናት ውስጥ ይጀምርና በሁለት ወይም በሦስት ወራት በዛ ከተባለ በስድስት ወር ውስጥ ህመምተኛው ከበሽታው ያገግማል፡፡

የሄፖታይተስ መንስዔዎች በሁለት ይከፈላሉ። ተላላፊ (ከኢንፊክሽን) ጋር የተያያዙ እና ከኢንፌክሽን ጋር ያልተያያዙ ናቸው፡፡ በአብዛኛው በሽታው የሚከሰተው ግን ከኢንፊክሽን ጋር በተያያዘው
መንስዔ ነው፡፡ ከኢንፊክሽን ጋር በተያያዘ ለሚመጣው በሽታ መንስዔ ከሚሆኑት ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው የአልኮል መጠጥ፣መድሐኒቶች፣ የኢንዱስትሪ ኬሚካሎች፣መርዛማ ነገሮች ይጠቀሳሉ፡፡አልፎ አልፎ የሰውነታችን የውስጥ መከላከያ (ኢሚዩኒቲ) ሲዛባ የእራሳችን የበሽታ መከላከያ ጉበታችንን ይጎዳውና «አውቶ ኢሚዩን» ሄፖታይተስ የተባለውን የጉበት መቆጣት ሊያስከትል ይችላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ምንም መንስኤው የማይታወቅ
የጉበት መቆጣት ሊከሰት ይችላል፡፡ ይህም «ክሪብቶጄኒክ» ሄፖታይተስ ይባላል፡፡

ሄፖታይተስ ቢ ምንድነው?
አብዛኛው ሄፖታይተስ የሚከሰተው በአምስት ዋና ዋና የጉበት ቫይረሶች ማለትም ሄፖታይተስ ኤ፣ቤ፣ሲ፣ዲ እና ኢ ተብለው በሚጠሩ የቫይረስ ዓይነቶች ሲሆን፤የእያንዳንዳቸው ባህሪና ምንነት የሚታወቀው በውስጣቸው ባለው ጄኔቲክ ማቴርያል ነው፡፡እነዚህ ቫይረሶች በሽታን የሚያመጡበት መንገድ ይለያያል፡፡ ሄፖታይተስ ኤ(A) እና ኢ(E) ከንጽህና ጉድለት ጋር በተያያዘ በተበከለ ውሃና ምግብ አማካኝነት የሚተላለፉ ሲሆን፤ ሄፖታይተስ ቢ፣ሲ እና ዲ
ልክ እንደ ኤች አይ ቪ ቫይረስ ከደምና ከደም ጋር በተያያዙ መንገዶች የሚተላለፉ ናቸው፡፡እነዚህ ቫይረሶች የሚራቡት ጉበት ውስጥ ሲሆን ፤ከተራቡ በኋላ ወደ ደም ዝውውራችን ይገባሉ። በእዚህ ጊዜ ሰውነታችን ቫይረሱን ለመዋጋት ፀረ ህዋስ (አንቲ ቦዲ) ያመርታል፡፡ሄፖታይተስ ኤ፣ ሲ፣ ዲ እና ኢ በተዘዋዋሪ መልኩ በምርመራ የሚገኙ ሲሆን ፤ እነዚህ ፀረ ህዋሶች በደማችን ውስጥ በምርመራ በመለየት የትኛው ቫይረስ እንደያዘን ለማወቅ ይቻላል፡፡ ሄፖታይተስ ቢ ከሌሎች ለየት የሚለው የቫይረሱን አካል (አንቲጅን) በምርመራ
ከደም ውስጥ በመለየት ቫይረሱ እንዳለብን በቀጥታ ማወቅ ይቻላል፡፡ በቫይረሱ ሽፋን ላይ ያለው አንቲጅን (ሄፖታይተስ ቢ ሰርፊስ አንቲጅን) በደም ውስጥ ከተገኘ ቫይረሱ እንዳለብን ያሳያል፡፡ ከቫይረሱ ውስጠኛው ክፍል የሚመነጭ አንቲጅን (ሄፖታይተስ ቢ ኢአንቲጅን) በምርመራ ከተገኘ በደም ውስጥ ያለውን የመራባት መጠንና የማስተላለፍ አቅሙን ከፍተኛነት ያሳያል፡፡
የቫይረሱ መጠን በላቦራቶሪ በደም ውስጥ በዝቶ በአንድ ሲሲ ከአሥር ሚሊዮን እስከ መቶ ሚሊዮን ከተገኘ የህመሙን ደረጃ ከፍተኛነት ያሳያል፡፡ አምስቱም የጉበት ቫይረሶች ድንገተኛ የጉበት መቆጣት ሲያመጡ ተመሳሳይ ምልክቶችን ያሳያሉ፡፡ ሄፖታይተስ ኤ እና ኢ ድንገተኛ የጉበት መቆጣት ያስከትሉና ጉበታችን በራሱ ጊዜ አገግሞ ሰውነታችንም ቫይረሶቹን ሙሉ በሙሉ ያስወግዳል። ስለዚህም በደም ውስጥ አይቆዩም፡፡ ሄፖታይተስ ቢ፣ ሲ እና ዲ ደግሞ ምንም ምልክት ሳያሳዩ በደም ውስጥ ለረዥም ጊዜ በመቀመጥ እየተራቡ ሄደው ስር የሰደደ የጉበት መቆጣት መንስኤዎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ከፍተኛ ደረጃ የደረሰ የጉበት በሽታና ካንሰርንም ሊያመጡ ይችላሉ፡፡ከአምስቱ ቫይረሶች ሄፖታይተስ ዲ ስንኩል በመሆኑ ለብቻው ሰውን የማጥቃት አቅም የለውም፡፡ ሰውን የሚያጠቃው ከሄፖታይተስ ቢ ጋር በመዳበል ወይም ሄፖታይተስ ቢ
የተያዘን ሰው ነው፡፡ ሁለቱ አብረው ሲከሰቱ የሚያስከትሉት ጉዳትም የከፋ ነው፡፡ሄፖታይተስ ቢ በአገሪቱ በከፍተኛ የጉበት በሽታና የጉበት ካንሰር መነሻነት በዋነኛነት የሚጠቀስ ቫይረስ ሲሆን ፤ከኤ እስከ ኤች የሚደርሱ ዝርያዎች (ጅኖታይፕስ) አሉት፡፡እነዚህ ዝርያዎች በተለያዩ የዓለማችን ክፍል የሚገኙ ሲሆኑ፤ የሚያስከትሉት የህመም መጠን አንዱ ከሌለው ይለያያል፡፡ አንዳንዶቹ በህክምና ቶሎ ሲድኑ አንዳንዶቹ ግን አይድኑም። በእዚህም ምክንያት ሄፖታይተስ ቢን ለህክምና አስቸጋሪ ያደርገዋል።

በሽታው ከሰው ወደ ሰው የመተላለፊያ መንገዶች
በሽታው የሚተላለፈው በቫይረሱ በተበከለ ደም፣ ልቅ የሆነ የግብረ ስጋ ግንኙነት፣የተበከሉ መርፌዎችና ስለታም ነገሮችን በጋራ በመጠቀም፣ በወሊድ ጊዜ ከእናት ወደ ልጅ በመሳሰሉት መንገዶች ከሰው ወደ ሰው ይተላለፋል።ቫይረሱ በበሽታው በከፍተኛ ደረጃ በተጠቁ ሰዎች ውስጥ መጠኑ ይለያይ እንጂ በማንኛውም ፈሳሽ የሚገኝ በመሆኑ በቀላሉ ከሰው ወደ ሰው እንዲተላለፍ ያስችለዋል፡ የሄፖታይተስ ቫይረስ ወደ ሰውነታችን ለመግባት ቀዳዳ ይፈልጋል፡፡ ምንም ጉዳት የሌለው ጤነኛ ቆዳ ውስጥ አልፎ አይገባም፡፡ ነገር ግን የዓይናችን የውስጠኛው ሽፋን ያለምንም ችግር ሊያስተላልፈው ስለሚችል ቫይረሱም ያለበት ፈሳሽ ዓይናችን ውስጥ ቢረጭ በበሽታው ለመያዝ መንገድ ይሆናል፡፡ ስለዚህ በቫይረሱ የተጠቁ ሕሙማንን የሚያስታምሙ የቤተሰብ አባላት የተላጠ ወይንም የተሰነጠቀ ማንኛውም ቁስል እጃቸው
ላይ ካለ በፕላስተር መሸፈን አለባቸው፡፡ማንኛውም ከሰውነት የሚወጣ ፈሳሽ (ላብንና ዕንባንም ጨምሮ) በጥንቃቄ መያዝና መወገድ አለበት፡፡ ቫይረሱ ወደ ሰውነታችን ሲገባ ከዘጠና እስከ ዘጠና አምስት ከመቶ የሚሆኑ ሰዎች ላይ የሰውነታችን መከላከያ ኃይል ቫይረሱን ሙሉ ለሙሉ አስወግዶ ቋሚ መከላከያ ይፈጥራል፡፡ ቫይረሱን ይዘው የሚቀሩት ከአንድ እስከ አምስት ከመቶ የሚሆኑ ሕመምተኞች ብቻ ናቸው፡፡ ቫይረሱ ካለባቸው ጥቂቶቹ ስር የሰደደ የጉበት መቆጣት ሲይዛቸው አብዛኞቹ ምንም ምልክት አያሳዩም፡፡ በአጠቃላይ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ካለባቸው ሰዎች ውስጥ ሃያ ከመቶ የሚሆኑት ብቻ ከፍተኛ የጉበት በሽታ (ክሮኒክ ሊቨርዲዚዝ) ይይዛቸዋል። ከእነዚህ ውስጥ እጅግ በጣም ጥቂቶቹ ከዓመታት በኋላ የጉበት ካንሰር ሊይዛቸው ይችላል፡፡የሲዲሲ (የተላላፊ በሽታዎች ማዕከል) ጥናት እንደ ሚያሳየው ኢንፌክሽኑ በብዛት የሚታየው ከሃያ እስከ አርባ ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ባሉ ሰዎች ሲሆን ሕፃናት
ላይ እንብዛም አይገኝም፡፡ ከአርባ ዓመት ዕድሜ በላይ ባሉ ሰዎች የበሽታው መጠን የመቀነስ አዝማሚያ ያሳያል፡፡ቫይረሱ ወደ ሰውነት በሚገባበት ወቅት ድንገተኛ የጉበት መቆጣት የሚያሳየው ምልክት የምግብ ፍላጎት መቀነስ፣ ማቅለሽለሽ፣ የሰውነት መቀነስ፣ ዐይን ቢጫ መሆን፣ በቀኝ
በኩል የላይኛው የሆድ ክፍል የህመም ስሜት የሚሰማ ሲሆን፤ ህመምተኛው ህክምና ከወሰደ በሦስት ወር ውስጥ ያገግማል፡፡ ስድስት ወር ከሞላው ግን ስር ወደ ሰደደ የጉበት በሽታ ይቀየራል፡፡

ሕክምናው
ለድንገተኛ የጉበት መቆጣት ምንም የሚሰጠው መድኃኒት የለም፡፡ ህመምተኛውም ከፍተኛ ካሎሪ ያላቸው ምግቦችን እንዲመገብና መልቲ ቫይታሚኖችን በመጠቀም ከበሽታው ለማገግም ይችላል፡፡ቫይረሱ በደሙ ውስጥ ያለበት አንድ ሰው ስለመድኃኒቱ ከመጨነቅ ይልቅ ጉብቱ ላይ ጉዳት ከሚያደርሱ ነገሮች ራሱን እየጠበቀ (እንደ አልኮል ያለ፣ ሐኪም ትዕዛዝ የሚወሰድ መድኃኒት፣ ያበሻ መድሀኒት) በተወሰነ ጊዜ ርቀት ቋሚ የህክምና ክትትል ቢያደርግ ይመከራል፡፡

ምንጭ:- ጤናችን

Advertisement