በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚፈፀሙ ውርጃዎች ግማሾቹ የሴቶችን ህይወት ለአደጋ ይዳርግሉ

                                                                                                     

በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ ከሚደረግ 55 ነጥብ 7 ሚሊየን የፅንስ ማስወረድ በአማካይ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት አስተማማኝ ያልሆኑ እና የሴቶችን ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥሉ መሆናቸውን አንድ ጥናት አረጋገጠ።

ጥናቱን ያካሄዱት የዓለም የጤና ድርጅት እና የአሜሪካ ጋትማከር ተቋም እንዳስታወቁት፥ በየዓመቱ 25 ነጥብ 5 ሚሊየን የፅንስ ማስወረድ ተግባራት ከተለመደው የጤና ሥርዓት ውጪ ወይም ባህላዊ ዘዴዎችን በመከተል ይፈፀማሉ። 

ከዚህ ውስጥ 97 በመቶ የሚሆኑት በአፍሪካ፣ በእስያ እና በላቲን አሜሪካ የሚፈጸሙ ሲሆን፥ 24 ሚሊየን ሴቶች ላይ ተፅእኖ እንደሚያሳድሩ ላንሴት የሕክምና መጽሔት ላይ ታትሞ የወጣው ጥናት ያስረዳል።

ጥናቱ እንደሚያመለክተው አፍሪካ በአብዛኛው አስተማማኝ የፅንስ ማስወረድ የማይታይባት በመሆኗ “በጣም ደካማ” እና ከፍተኛ የሞት መጠን የሚታይባት አህጉር ተብላ በመመደብ እጅግ አስከፊ ሁኔታ ላይ ተቀምጣለች።

ላቲን አሜሪካ ከአፍሪካ የጤና ስርዓት ይበልጥ ውጤታማ በመሆኑ የፅንስ ማስወረድ ሁኔታው “በጣም ደካማ” ከሚለው ይልቅ “ደካማ” በሚለው ተመድቧል።

ጋትማከር እንደገለጸው ብዙ ገዳቢ ሕጎች በሌላቸው፣ ከፍተኛ የኢኮኖሚ እድገት እና የጤና መሰረተ ልማቶች ባላቸው ሀገሮች ውስጥ ጥንቃቄ የተሞላበት የፅንስ ማስወረድ ተግባር ታይቷል።

ይህም የሕግ ማዕቀፍ እና አጠቃላይ የሀገራቱ ልማት የተሻለ ውጤት ለማምጣት የላቀ ሚና እንዳለው ተገልጿል።

የዓለም ጤና ድርጅት በበኩሉ በየዓመቱ 47 ሺህ የሚያህሉ ሴቶች በፅንስ ማስውረድ ምክንያት ህይወታቸውን ያጣሉ ያለ ሲሆን፥ ይህም በዓለም ዙሪያ ከሚያጋጥሙ የእናቶች ሞት መካከል 13 በመቶውን ድርሻ ይይዛል ብሏል።

በዓለም ጤና ድርጅት የጥናቱ ዋነኛ አዘጋጅ ቤላ ጋናትራ፥ የእርግዝና መከላከያ ማግኘት፣ ተደራሽነት እና የመግዛት ዓቅምን መጨመር ያልተፈለገ እርግዝናን በመከላከል ፅንስን የማስወረድ ተግባር ይቀንሳል ነው ያሉት። 

ነገር ግን ይህንን ዘዴ ለመፈፀም የሚያስችል ስትራቴጂ ማዘጋጀትና የፅንስ ማስወገድ ተግባራትን መቆጣጠር አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል።

በሰለጠነ ባለሙያ አግልግሎት በመስጠት እና በዓለም የጤና ድርጅት የተደገፈ ዘዴን ከሚጠቀሙ ባደጉ አገሮች ከሚገኙት 10 ፅንስ የሚያስወግዱ ሴቶች ውስጥ ዘጠኝ የሚሆኑት በጥሩ ሁኔታ እንደሚከናወን ጥናቱ አመላክቷል።

ለዚህም ጥናቱ እንደሚያመላክተው ከሆነ በ57 ሀገራት በጥያቄ መሰረት ከሚደረግ የፅንስ ማስወገድ 90 በመቶ በጥሩ ሁኔታ ተፈፅሟል። 

ይሁን እንጂ በ62 ሀገራት ውስጥ ያለጥንቃቄ ከተካሄደው የፅንስ ማቋረጥ 25 በመቶ የሚሆኑት ብቻ በጥሩ ሁኔታ ሲከናወን፥ የተቀረውን የሴቶች ህይወት ወይም ጤና አደጋ ላይ እንደጣለ ተገልጿል።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement