NEWS: የሳዑዲ ንጉስ ሴቶች መኪና እንዲነዱ የሚፈቅድ አዋጅ አወጡ

                                                      

የሳዑዲ አረቢያ ንጉስ ሳልማን የአገሪቱ ሴቶች መኪና እንዲነዱ የሚፈቅድ ህግን አወጡ።

ሳዑዲ አረቢያ ሴቶች መኪና እንዳያሽከረክሩ የምትከለክል ብቸኛዋ አገር ናት።

በአገሪቱ የመንጃ ፈቃድ ማውጣት የሚፈቀድላቸው ወንዶች ብቻ ሲሆኑ፥ ሴቶች መኪና ሲያሽከረክሩ ከተገኙ ቅጣት እና እስር ይጠብቃቸዋል።

ሴቶች እንዲነዱ የወጣውን አዋጅ በያዝነው ዓመት ሰኔ ወር ላይ መተግበር ይጀምራል ነው የተባለው።

በርካቶች ይህን የሳዑዲን ውሳኔ ያደነቁ ሲሆን፥ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሴቶች መብትን ከማስተዋወቅ አንፃር አወንታዊ እርምጃ ነው ብለዋል።

አስተያየታቸውን ለሬውተርስ የሰጡ የሳዑዲ ሴቶች በበኩላቸው ለዓመታት ለመንዳት ሲያልሙት የነበረውን የመኪና ዓይነት ገዝተው ለማሽከርከር መጓጓታቸውን ነው የተናገሩት።

በርካታ የአገሪቱ ዜጎች ውሳኔውን ቢያደንቁም፥ የአገሪቱ መንግስት የሼሪአ ህግን የሚፃረር ውሳኔ ነው ያሳለፈው ሲሉም የከሰሱ አሉ።

በሳዑዲ በተለይም በከፍተኛ ደረጃ የተማሩ ሴቶች ይህንን ህግ ሲጠብቁ መኖራቸው ይነገራል።

በአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ የወንዶችን ያህል ሚና እንዳይጫወቱ የተነፈጉት ሴቶች መኪና ማሽከርከር በመከልከላቸው ብቻ የኑሮ ወጪያቸው እንዳናረ የሚናገሩ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች አሉ።

በአገሪቱ ሴቶችን ከቦታ ቦታ በመኪና ለማንቀሳቀስ ብቻ የተቀጠሩ በብዛት የእስያ አገራት ዜግነት ያላቸው 800 ሺህ ሾፌሮች በአገሪቱ ይገኛሉ።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

 

Advertisement