NEWS: ከዓለም ሴት ቢሊየነሮች ቀዳሚውን ስፍራ የያዙት ባለፀጋ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ

                                         

ከዓለም ሴት ቢሊየነሮች ቀዳሚውን ስፍራ የያዙት ፈረንሳዊቷ ባለፀጋ በ94 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።

ህልፈተ ህይወታቸውን የገለጹት ቤተሰቦቻቸው ሊሊያን ቤተንኮርት የተባሉት እኝህ ባለፀጋ ቤታቸው ውስጥ ምሽት ላይ መሞታቸውን ተናግረዋል።

የታዋቂው ሎሪያል የውበት መጠበቂያ ምርቶች (የኮስሞቲክስ) ኩባንያ ከአባታቸው ወራሽ እና ባለቤት ነበሩ።

ሟች የኩባንያው መስራች ኤዩጅን ሹለር ልጅ ናቸው።

ፎርብስ እና ብሉምብርግ ባወጡት መረጃ ቤተንኮርት ከዓለም ሴት ቢሊየነሮች ቀዳሚ ሲሆኑ፥ የሃብታቸው መጠንም 44 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ይደርሳል።

በእርግጥ ሀብታቸውን በተመለከተ ቢቢሲ 33 ቢሊየን ዩሮ ወይም 30 ቢሊየን ፓውንድ አልያም 40 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር በሚል አስቀምጦታል።

በአሁኑ ወቅት ቤተሰባቸው የሎሪያል ግሩፕ 33 በመቶ ድርሻ ባለቤት ነው።

ሊሊያን ቤተንኮርት በማረፋቸው ጥልቅ ሀዘን እንደተሰማቸው እና ሁሉም ቤተሰብ እንዲሁም የድርጅት ሰራተኛ ለኩባንያቸው ስኬት የበለጠ እንዲሰሩ የሎሪያል ፕሬዚዳንት ጂያን ፓውል አጎን ተናግረዋል።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement